ዛሬ ምሽት በአዉሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ይካሄዳሉ
ከምድብ 1 እሰከ 4 የተደለደሉ ቡድኖች የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ሲሆን ከነዚህ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች መካከል በምድብ አንድ ባየርንሙኒክ ከ ማንቸስተር ዩናይትድ በአሊያንዝ አሬና እንዲሁም በምድብ ሁለት በኤምሬትስ አርሰናል ከ ፒኤስቪ ኤይንድሆቨን ጋር የሚያደርጉት መርሃግብር ልዩ ትኩረትን ስቧል ።
ታሪክ ከማይዘነጋቸዉ የቻምፒየንስ ሊግ የፍፃሜ ወድድሮች መካከል አንዱን በባርሴሎና እኤአ በ1999 ድራማዊ ትዕይንት ያስመለከቱን ባየርንሙኒክ እና ማንቸስተር ዩናይትድ የሚያደርጉት የምሽት 4:00 ጨዋታ ከወዲሁ በብዙዎች በጉጉት ይጠበቃል ።
በ 34 የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች ያልተሸነፈው እና በሦስት ተከታታይ የዉድድር ዓመታት ስድስቱንም የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዎች በማሸነፍ የክብረወሰን ባለቤት የሆነው ባየርንሙኒክ የዉድድር ዓመቱን በጥሩ ሆኔታ ጀምሮ፣ የአዉሮፓ ሻምፒዎንስ ሊግ ዋንጫን ለማንሳት የያዘዉን ዉጥን ለማሳካት የመጀመሪያ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታዉን በሜዳዉ ማንቸስተር ዩናይትድን በማስተናገድ ይጀምራል ።
በዉጤት ማጣት እና በወሳኝ ተጫዋቾች መጎዳት፣ ከአንዳንድ ተጫዋቾች ጋር በተፈጠረው አለመግባባት አዲሱ የዉድድር ዓመት አጀማመር ያላማረላቸዉ ኤሪክ ቴንሃግ፣ ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ አውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዉድድር የመለሱትን ማንቸስተር ዩናይትድን ይዘዉ ከዚህ ቀደም ለ 3 ዓመታት የተስፋ ቡድኑን ያሰለጠኑለት ባየርንሙኒክን ለመግጠም የቡድን ስብስባቸዉን በመያዝ ወደ ጀርመን አቅንተዋል ።
ሁለቱ ክለቦች ከዚህ ቀደም 11 ጊዜ በአዉሮፓ ሻምፒዮንስሊግ የተገናኙ ሲሆን ባየርንሙኒክ 5 ጊዜ ሲያሸንፍ ፣ ማንቸስተር ዩናይትድ 2 ጊዜ አሸንፏል ። ቀሪ 5 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ዉጤት ተጠናቀዋል ።
በባለሜዳው ባየርንሙኒክ በኩል ራፋኤል ጉሬሮ እና ኪንግስሌ ኮማን ከጉዳት አገግመዉ ልምምድ መስራት በመጀመራቸው ለምሽቱ ጨዋታ የሚደርሱ ሲሆን ግብ ጠባቂው ማኑኤል ኑዌር ግን በጉዳት ከዛሬዉ ጨዋታ ዉጪ ሆኗል ።
በማንቸስተር ዩናይትድ በኩል ባሳለፍነዉ ሳምንት ጉዳት ያስተናገዱት አሮን ዋን ቢሳካ እና ሃሬ ማጓዬርን ጨምሮ ከጉዳት በማገገም በትናንትናዉ እለት ልምምድ መስራት የጀመሩት ማሰን ማዉንት፣ ኮቢ ማይኖ ፣ ራፋይል ቫራን እና ሶፊያን አምራባት ወደ አሊያንዝ አሬና ባቀናዉ ስብስብ ዉስጥ አልተካተቱም ።
በሌላ ጨዋታ ለስድስት ዓመታት ከአዉሮፓ ሻምፒዎንስ ሊግ ርቆ ቆይቶ የተመለሰው አርሰናል፣ ለአራት ዓመታት ከሻምፒዮንስ ሊጉ ርቆ የተመለሰዉ ፒኤ.ስቪ ኤይንድሆቨንን በኤምሬትስ ያስተናግዳል ።
በከፍተኛ የገንዘብ ዉጪ አዳዲስ ፈራሚዎችን ወደ ስብስቡ የቀላቀለዉ የሚኬል አርቴታዉ ቡድን ፣ በተጠናቀቀው የዉድድር ዓመት በእንግሊዝ ፕሪሚዬርሊግ ያስመለከተዉን ጠንካራ አቋም ዘንድሮም በዉስጥ ዉድድሮች እና በአዉሮፓ መድረክ ለመድገም እያለመ የሻምፒዮንስሊግ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታውን ይጀምራል ።
ፒኤስቪ በአሰልጣኝ ፒተር ቦዥ እየተመራ በኤርዲቪዜዉ ያደረጋቸዉን አራቱንም ጨዋታዎች አሸንፎ የዉድድር ዓመቱን በጥሩ ሁኔታ በመጀመር ሊጉን እየመራ ይገኛል ።
እኤአ ከ1998 እስከ 2017 ለተከታታይ 19 ዓመታት በሻምፒዮንስ ሊጉ ሲሳተፍ ቆይቶ ከዉድድሩ ለግማሽ ደርዘን ዓመታት ያኽል ርቆ በተመለሰዉ የአርሰናል ስብስብ ዉስጥ ብራዚላዊዉ የፊት መስመር ተጫዋች ጋብሬል ሄሱስ በማንቸስተር ሲቲ ቤት ሳለ በቻምፒዎንስ ሊጉ በ 38 ጨዋታዎች 28 ጎሎችን አስቆጥሯል ።
ይህም ጨዋታ የማድረግ እና ግብ የማስቆጠር ልምዱ የሰሜን ለንደኑን ክለብ በእጅጉ ሊጠቅመዉ እንደሚችል ተገምቷል ።
ምሽት 4:00 ሲል በሚጀምረዉ ጨዋታ በአርሰናል በኩል ጋብሪኤል ማርቲኔሊ ለጨዋታው የመድረሱ እድል ጠባብ መሆኑ ሲገለፅ ጁሪያን ቲምበር፣ ቶማስ ፓርቴ እና ሞሃመድ ኤልኒኒ ከምሽቱ ጨዋታ ዉጪ መሆናቸውን ክለቡ አረጋግጧል ።
በፒኤስቪ በኩል ኖአ ላንግ፣ አርማንዶ ኦቢስፖ፣ ፍሬድሪክ ኦፔጋርድ እና ማዉሮ ጁኒዬር በጉዳት አይሰለፉም።
ሌሎች የምሽት መርሃብሮችን ከስር በምስሉ ላይ ያገኙታል ።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
More Stories
ሮድሪጎ ቤንታንኩር ከእግር ኳስ ጨዋታዎች ታገደ
በቀቤና ልዩ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ 5ተኛ አመት ምስረታን ምክንያት በማድረግ ማህበረሰብ አቀፍ የማስ ስፖርት በወልቂጤ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል
የአካል ብቃት እንቅስቃሴን ባህሉ ያደረገ ጤናማና ንቁ ማህበረሰብ ለመፍጠር እየተሠራ መሆኑ ተገለፀ