ከሀዋሳ እስከ ጥያ

በደረሰ አስፋው

እነሆ መንገድ! ወደ ውስጥ ገባ ብሎ ካለው መኖሪያ ቤቴ ጨፌ መንደር ወጣ እያልኩ ነው። የሀምሌ ክረምት ከበድ ብሏል፡፡ የማለዳው ሰማይ ጠቋቁሯል፡፡ የነጎድጓዱ ጩኸትም ጆሮ ይሰነጥቃል፡፡ ውሽንፍር የቀላቀለው ብርድ ልብስ ደረብረብ ላላረገ ሰው ውስጥ ገብቶ ያንሰፈስፋል፡፡ የዝናቡ ሁኔታ ስላሰጋኝ እርምጃዬ የሶምሶማ ሩጫ አይነት ነው፡፡

ደረስኩ ታክሲያችን ረጅም ዕድሜን ያስቆጠረችው ባለሰማያዊ ቀለሟ ሚኒ ባስ ናት። የመንገደኛው ብዛት አገልግሎት ከሚሰጡ ታክሲዎች ጋር አልተመጣጠነም። ከበድበድ ያለው ክረምት ታክሲዎችን ጭምር ሳይጫጫናቸው አልቀረም፡፡ ተጨማሪ ታክሲዎችን ማየት አልተቻለም፡፡ ወያላው ከላይ ፀጉሩ እስከ ታች ጥፍሩ ግጥም አድርጎ ለብሶ እጁን ኪሱ ከትቶ አሮጌ “መናኸሪያ መናኸሪያ!” እያለ ይጣራል፡፡

አንዳንድ እየተባለ ሚኒባሷም ከገደብ በላይ ሞላች፡፡ አንዳንድ ሰዎች፣ “ይህቺ ታክሲ አሁንም አለች? ችላስ ትወስደናለች?” እያሉ ይቀላለዱባታል ከማርጀቷ የተነሳ፡፡ የጭነቷ ልክ ከመጠን ያለፈ በመሆኑ መስጋታቸውም አልቀረም፡፡

“ጠጋ ጠጋ! ሥጋ ያላችሁ ደግሞ ደቀቅ ደቀቅ ያሉትን ብትታቀፉዋቸው ደስ ይለኛል። አዎ ‘ብቻህን አትብላ’ ይላል ቅዱስ ቃሉ!” ይላል ወያላው፡፡ ኣለ ልክ የጫነው አላረካውም፡፡ በወያላው ድፍረት የተሞላበት አባባል ተሳፋሪዎች ከመበሳጨት ይልቅ ይዝናናሉ። “ጭራሽ እንተዛዘልላችሁ? እሱ ነው የቀራችሁ” ሲሉ አንድ አዛውንት፣ “ቀበል አድርገው መቼ ከሰው ይቆጥሩናል” በማለት ንዴት በቀላቀለ ስሜት ተናገሩ፡፡

ወያላው ግን የምፈልገውን ያህል ጠጋ ጠጋ አላላችሁም በሚል ከረር ያለ ውዝግብ አስነሳ። “የት እንሂድልህ ከዚህ በላይ?” ሲለው አንዱ ሌላውን ተቀብሎ፣ “ወይኔ ሀገሬ! እውነት ይኼን ሕዝብ ወያሎች የሚመሩትን ያህል ሌሎች ይመሩታል?” ብሎ አሸሞረ። አሽሙሩ እንደተሳካለትና እንዳልተሳካለት ሊያጣራ ዙሪያ ገባውን ቃኘ።

ከስንት ጭቅጭቅና ንትርክ በኋላ ነው፡፡ የወያላው አቀማመጥ የሊቀመንበር ይመስል ነበር፡፡ እንደሊቀመንበር ተቀመጠ። ታክሲያችን መንቀሳቀስ ጀመረች። በትርፍ ገንዘቡ ወያላው ገዝቶ የለጠፋቸውን ጥቅሶች በማንበብ ሰው ‘ቢዚ’ የሆነም ይመስላል። “መተዛዘን ጠፍቶ ግራ ስንጋባ፣ የስሙኒ እንቁላል አስራ ሦስት ብር ገባ!” ብሎ አንደኛው ተሳፋሪ ጮክ ብሎ አነበበ። ሌላውም ሌላ ያነባል፡፡

የተቀረው ይስቃል። ሌላው ልክ ነው ይላል፡፡ እኔ ለማንበብ እድሉን አላገኘሁም ሰሚ ግን ሆኛለሁ፡፡ ተደራርበን ከመቀመጣችን የተነሳ ቀና ብዬ ባላነብም መስማት ግን አልተሳነኝም፡፡

ታክሲዎች ላይ የሚለጣጠፉ፣ ጥቅሶችን የማንበብ ልማድ አለኝ፡፡ አዝናኝ፣ አስተማሪ ሌሎቹ ደግሞ ውስጠ ወይራ የሆኑ ሸንቆጥ የሚያደርጉ ስላሉ ሳቢዎች ናቸው፡፡ እንዲህም እንዲያ እያልን እንደ ኤሊ በምታዘግመው ዕድሜ ጠገብ ሚኒባስ አሮጌው መናኸሪያ አንድ ሰዓት ተኩል ደረስን፡፡

ጉዞው አልተገታም ትኬት ቆርጨ ቡታጀራ ወደሚሄደው መኪና አቀናሁ። እንዳለመታደል ሆኖ 36 ሰው በሚጭነው ቅጥቅጥ አይሱዙ መኪና ውስጥ ሶስተኛው ተሳፋሪ ሰው ሆንኩ፡፡ ሌላ አማራጭ እንዳልፈልግ 175 ብር ከፍያለሁ፡፡ በትግስት ለመጠበቅ ወስኜ ተቀመጥኩ፡፡ እንደሰጋሁት ግን አልሆነም፡፡ ጥቁር የለበሱ በርከት ያሉ ወንድና ሴት ወጣት እና ሽማግሌ ለቀስተኞች በአንድ ጊዜ መኪናውን ሞሉት፡፡ እንዲያውም ቀድመን የገባነውን በትርፍነት ተቆጥረን ለማስወረድ የዳዳቸውም አልጠፉም፡፡

የቆረጥኩትን ትኬት በእጄ ጨብጫለሁ፡፡ አንዳንዶች ገባ ወጣ እያሉ አይናቸውን እኔ ላይ ይወረውራሉ፡፡ እኔም ከመገረም ባለፈ እልህ የተሞላበት ንዴት ውስጥ ገባሁ፡፡ እንደሌባ ይጠቋቆሙብኝ ጀመር፡፡ አፍ አውጥተው ውረድ ባይሉኝም እንድወርድ የሚያደርጉ ጸያፍ ባህሪያትን ተመለከትኩባቸው፡፡

ከብዙዎች መካከል ቁም ነገረኛ አልጠፋምና በእድሜ ጠና ያሉ ሰውዬ ወደ ውስጥ ገቡና “መኪናው በሩን ሲከፍት ገብቶ የተቀመጠ ሰው እንዴት ውረድ ይባላል? ነውር አይደለም” ብለው በሰዎቹ ላይ ሲያንባርቁባቸው መኪናው ውስጥ የነበረው ድባብ በአንድ ጊዜ ተለወጠ፡፡ እኔም መቼም በቀናት መካከል የሚያጋጥም ክስተት ነው በማለት እራሴን በራሴ አጽናናሁ፡፡ ሾፌሩም ከመቅጽበት ገብቶ መኪናውን አንቀሳቅሶ ጉዟችን ከረፋዱ 4፡30 ሰዓት ወደ ቡታጅራ ተጀመረ፡፡ በማለዳው ከበድበድ ብሎ የነበረውም ሰማይ ዘንቦ ባይወጣለትም ፈገግ ብሏል፡፡

እርስ በርስ እያደር የባሰብን መጨካከንና ራስ ወዳድነት ከየት የመጣ ነው እባካችሁ? ብላ ከኔ ጋር ቀድማ የተቀመጠች የኔው ቢጤ እጣ ፈንታ የገጠማት ወጣት ሴት በስሜት ሐሳቧን ሰነዘረች፡፡ ጥያቄውን ለማን እንደምትጠይቅና ማን እንደሚመልስላት ግን የተገነዘበች አይመስልም፡፡ ሁሉንም ነገር በትዝብት ስትመለከት ስለነበረ ነገሩ ውስጧን የቆረቆራት ስለመሆኑ መረዳት ይቻላል፡፡

አንዱ ጣልቃ ገብቶ የጨዋታውን መስመር ይቀይሳል። “ያ እዛ ጋ የማየው ሀይቅ ምንድነው?›› በማለት የብዙዎችን ሀሳብ በእንጭጩ እንዲቋጭ አደረገ፡፡ ይህ ባይሆንማ ነገሩ ሌላ አዝማሚያ ይኖረው ነበር ብዬ ገመትኩ፡፡ ሀሳቡ እውነት ሀይቅ የመሰላቸው አንዳንዶች ግን አጨንቁረው በመስታወት ማየታቸውም አልቀረም፡፡ እያዩም ይጠይቃሉ፡፡ አጠገቤ ነጠላ ተከናንባ የተቀመጠች ወጣት የስላቅ ሳቅ እየሳቀች መለሰችላቸው።

“በሞትኩት! ይቅር በሉኝ አደራችሁን” ሲልም ሀሳቡን ያስቀየረው ወጣት ተናገረ፡፡ በነገሩ የተከፉትም ቢሆን ከማጉረምረማቸው በላይ ወጣቱን በነገር ሸንቆጥ ማድረጋቸው አልቀረም፡፡ ቀጠል አድርገውም “የዚህ ዘመን ልጆች ታላላቅን ማክበር የለ ያው እኩል ቆራሽ ሆናችሁ ብቻ ግዜው ያመጣብን ጣጣ ነው”፣ ብለው ግዜውንም መውቀሳቸው አልቀረም፡፡

“ኧረ አይዞዎት! ያሻዎትን መናገር ሕገ መንግሥታዊ መብትዎ ነው” ሲላቸው “እሱማ መቼ ጠፋኝ፤ “ሕጉን እኖር ብዬ ፅድቁ እንጂ እየጠፋኝ፤” አሉትና አፋቸውን በነጠላቸው ከለል አድርገው የትዝብት ሳቅ ሳቁ። ቅኔያቸው የገባውም ፈገግ አለ፡፡ በነዚህም ቢሆን ትንሽ ዘና ማለታችን አልቀረም፡፡ ጉዟችን ቀጥሏል። ጥቁር ውሃ፣ ሻሸመኔ፣ አርሲ ነጌሌን አልፈን ቡልቡላ ደረስን፡፡

በመሃል መሃል ክረምቱ አረንጓዴ ያለበሰውን ውብ ምድር እተመለከትን ዘና ማለቱንም አልዘነጋነውም፡፡ ወያላውም የጉዞ ትኬታችንን እንደመሰብሰብ ወሬያችን በልጦበት አፍ አፋችንን ያያል። “እንካ እንጂ ተቀበል! ትኬት ተቀበሉን ስንል በልመና፣ ስሙን ስንል ልመና፣ ምንድነው የሚሻለን ግን?” አለ አንድ ወጣት ለወያላው ትኬቱን እያቀበለው። ለጨዋታ እንጂ ትኬቱ ግን ለረዳቱ አስፈላጊው አልነበረም፡፡

ይኼን ጊዜ ጋቢናውንና እኛን የሚለየንን መስታወት ተደግፋ ውሽቅ ብላ የተቀመጠች ከመኪናው እንድትወርድ ተፈርዶባት የነበረች ልጅ አንገቷን ብቅ አድርጋ፣ ‹‹የሚሻለውማ መመነን ነው። የሰው ልጅ ወደመጣበት ወደዛች ኤደን ገነት እስካልተመለሰ ድረስ እዚህ ምድር ላይ ፍትሕ ልትሰፍን አይቻላትም። እውነትም እርቃኗን ሐሰትም የእውነትን ልብስ እንደለበሰች ነገር ሁሉ መቀጠላቸው አይቀሬ ነው” አለችው ተናጋሪውን ከሌሎቻችን ይልቅ እያስተዋለች የልቧን ለመናገር ዕድል ስላገኘች።

“ሴትዮ ፍልስፍናውን አቆይና ትኬቱን ስጭኝ” በማለት ሌላ የጨዋታ ምዕራፍ ሊከፍት ቢዳዳውም የወረደበት ስድብ የማይነገር ሆነ። ከመሀላችን አንዱ፣ “በቃ እኔ ላስታርቃችሁ” ብሎ ወያላውን ዝም ባያሰኘው ኖሮ ብሶት የወለደው ስሜት ምን እንደሚያሳየን መገመት ከባድ ነበር። ምነው እንዲህ ሁሉም ነገር ለግምት ከብዶን ውረድ እንውረድ በቁልቁለቱ ሆነብን ነገሩ? በማለት ጥሉን ያለዝበው ጀመር፡፡

ወደ መዳረሻችን ቡታጀራ ተቃርበናል። አንደኛው ተሳፋሪ ‹‹የመንገዱ የፍተሻ ነገር ነፃ ባይሆን ኖሮ እንዲህ በጊዜ አንገባም ነበር ብሎ ወሬ ጀመረ። የወዲያኛው ተቀብሎ፣ “አንተን የሚገርምህ የጉዞው ነገር ብቻ ነው? አስተሳሰባችንና አመለካከታችንስ? ስንት ያልተነካ ስንት ያልተሠራ ሥራ እያለ ልክ እንደ መኪና መንገዱ ጥቂት የሥራ ዘርፎች ላይ መጣበባችንስ?” ይለዋል።

“ይኼው እንደምትሉት በረባ ባልረባው ተፋፍገን በኤሊ ፍጥነት እየተሳብን ‘ከመቆም ይሻላል’ እንላለን፤›› ብላ አንዲት ቆንጂት አስተያየቷን ሰጠች። ያለነው የቡታጀራ ከተማ መግቢያ እሪንዛፍ ወንዝን ድልድዩ አለፍ ብለናል፡፡ መኪናው ባልታወቀ ምክንያት ከፊት ለፊቱ የቆሙትን መኪናዎችን ተከትሎ ቆመ፡፡ ወያላው ወርዶ መንገዱ የተዘጋጋበትን ምክንያት አጣርቶ ሲመጣ፣ “ግጭት ነው። የሚቸኩል ካለ ወርዶ ማዝገም ይችላል” ብሎን አረፈው። አብዛኞቻችን የሆዳችንን በሆዳችን ይዘን ወረድን።

እንዲህ የሆድ ሆዳችንን ስናወጋ የሕይወት ማስተዛዘኛ ሆኖልን እስከ ቡታጀራ የነበረውን ጉዟችንን አጭር አድርጎልናል፡፡ የተናደደም ቢሆን እኔን ጭምር በጉዟችን ብዙ የከፋን አልነበርንም፡፡ ለቀስተኞችም የለበሱትን የሀዘን ጥቁር ልብስ በወጉ እያስተካከሉ ወደ ግራ ታጥፈው በሩቅ ወደ ሚታየው ድንኳን አቀኑ፡፡ እኔም የጉዞዬ መዳረሻ ከቡታጀራ አለፍ ብሎ ወደ ሶዶ ወረዳ ቡኢ ነውና ሌላ መኪና ላይ ለመሳፈር ባለሶስት እግር ባጃጅ ይዤ ወደ ቡታጀራ መናኸሪያ አቀናሁ፡፡

እዚህ ደግሞ እንደመታደል ሆኖ የሞላች ዶልፊን መኪና ላይ ነበር ያጋጠመኝ፡፡ እኔ እንደገባሁ “አንተን አይደል የምንጠብቅህ” በማለት ረዳቱ የመኪናዋን በር ዘግቶ የቡታጅራን ሰሜን አቅጣጫ ይዛ መክነፍ ጀመረች፡፡ እርሻዎች ሜዳውና ሸንተረሩ አረንጓዴ ለብሷል፡፡ አልፎ አልፎ በእርሻ ስራ ላይ የተጠመዱ አርሶ አደሮችንም ተመለከትኩ፡፡ ከዚህ ቀደምም በነበረኝ የጉዞ ማስታወሻ ዙሪያ ገባውን ስላነሳሁ መድገሙ አላስፈለገኝም፡፡

ቡኢ ከተማ ከቀኑ 10፡00 ደረስን። ከተማዋ ከወትሮው በተለየ ሞቅ ደመቅ ብላለች። ሆቴሎቿና ካፍቴሪያዎቿ ተበራክተዋል። ሰዓቱ ወደ መራኝ ወደ አንዱ ሆቴል ጎራ አልኩ። በረንዳቸው ሳይቀር በሰው ተሞልቷል። ይበላሉ ይጠጣሉ ይዝናናሉ፡፡ ሙዚቃው ካፍ እሰከ ገደቡ ተለቆ ገሚሱ አብሮ ያንጎራጉራል። ሌላው ከትከሻ ለመውረግረግ ይዳዳዋል፡፡ እኔ ግን አልበላሁ አልጠጣሁ ሰውነቴ በጉዞ ዝሎ ለየት ያለ ሰው ሆኛለሁ፡፡

ወንበር ፈላልጌ እንደተቀመጥኩ ከጎኔ የነበሩ እንብላ ሲሉ በኢትዮጵያዊነት ባህላችን ጋበዙኝ፡፡ እኔም አላቅማማሁም ያዘዝኩት የመጣ በመሆኑ ብቻ መብላት ንፉግነት ነው በሚል አብሬ ተቀላቀልኩ፡፡ ከምግቡም ከሚጠጣውም ሁሉም ባሻው አይነት ቀማምሷል፡፡ በመጨረሻ ግን ጋባዥ እኔ ነኝ ብሎ አንዱ አሻፈረኝ አለ፡፡ የኔም ሂሳብ አብሮ ተከፍሎ ነበርና አመስግኘ ተለያየን፡፡

ከስራየ ባህሪ የተነሳ በ2ኛው ቀን ጉዞዬን ያደረኩት ወደ ጥንታዊቷ ከተማ ጥያ ነው። ጥያ የታሪካዊ የጥያ መካነ ቅርስ ትክል ድንጋዮች መገኛ ነች፡፡ በውስጧ አቅፋ በያዘቻቸው ቅርሶቿ በዓለም ታዋቂ ከተማ አድርገዋታል፡፡ በዩኒስኮም በዓለም ቅርስነት ተመዝግባለች፡፡ እንዳለመታደል ሆኖ ይህን ታሪካዊ ስፍራ አቅፋ የያዘችው የጥያ ከተማ ስሟ በዓለም በገነነው ልክ የተሰራች ከተማ ሆና አላገኘኋትም፡፡ ለቱሪስቶች አይደለም ላላፊ አግዳሚው የሚሆን ማረፊያ ለማግኘት እንኳ የከበደ ነው፡፡

ሌሎች ስራዎችን ከሰራሁ በኋላ ወደ ትክል ድንጋዮችም ጎራ ብዬ ቃኘት ማድረጌ አልቀረም፡፡ የጥበቃ ሰራተኞችና አስጎብኚዎች ከውጭ ተቀበሉኝ፡፡ በተንጣለለው ሜዳ ላይ ከቅርብ ርቀት የሚታዩትን ትክል ድንጋዮች ተመለከትኩ፡፡ ቀረብ ብየም በአስጎብኝው የተወሰኑ መረጃዎችን ለማግኘት ቻልኩ፡፡ የቅርሱ ታሪካዊነት አስገራሚ ነው፡፡ ረጅም ዕድሜ ያስቆጠረ እንደሆነም ተረዳሁ፡፡

ይሁን እንጂ ቅር የተሰኘሁበት ነገርም አልጠፋም፡፡ የቅርሱ ደህንነት ከአስጎብኝዎችና የጥበቃ አካላት ውጪ ዋስትና የሰጠው አካል እንደሌለ መታዘብ ቻልኩ፡፡ ጎብኝዎችም በአካባቢው የማረፊያ ስፍራ ባለመኖሩ ለቆይታ ጊዜያቸው ፈተና እንደሆነባቸው ነው አስጎብኝው የገለጸለኝ፡፡

በቅጥር ግቢው ውስጥ እዚህም እዛም ተሰብረው የወደቁ ትክል ድንጋዮች የተመልካች ያለህ የሚሉ ይመስላል፡፡ ስለ ታሪካዊ ቅርሱ መረጃ ለማግኘት አዳጋች ነው። የቅርሱን ታሪካዊነት የሚመጥን ሙዚየም የለም፡፡ በፈረንሳይኛ ከተጻፈ መጽሃፍ ውጪ በአማርኛ የተጻፈ አለያም የተሰነደ ነገር የለም። ቅርሱን እንደተመለከትኩ ሁለት የተቀላቀሉ ስሜቶች ነው የተሰማኝ፡፡ ታሪካዊ ቅርሱ በሀገሬ ኢትዮጵያ መገኘቱ ደስታ፣ ለቅርሱ የተሰጠው ትኩረት ማነስ ደግሞ የሀዘን ስሜት እንዲሰማኝ ነው ያደረገኝ፡፡

ያም ቢሆን በተንጣለለው ሜዳ ላይ ቆመውም የወዳደቁትንም ይሁን የተሰባበሩትን በካሜራየ አስቀርቼ ስፍራውን ተሰናበትኩ። ጉዳዩን አስመለክቼ ለማነጋገር የፈለኩትን አካል ማግኘት አልተሳካልኝም፡፡ ሌሎች የመስክ ስራዎቼን ሰራርቼ የጥያ ትክል ድንጋይ ደህንነት በምናቤ እየሳልኩ ጉዞዬ ወደ ሀዋሳ ሆነ፡፡