“ዓለምን የፈጠረው መስከረም ፩ ነው”

 በቦጋለ ወልዴ

በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዓመታት ሁሉ በአራት መደባት ይሸጋገራሉ። እነኚህም፡- ዘመነ ማቴዎስ፣ ዘመነ ማርቆስ፣ ዘመነ ሉቃስ እንዲሁም ዘመነ ዮሐንስ ይባላሉ፡፡

እንግዲያው ጳጉሜ 6 ቀን ስናጠናቅቅ እንኳን ለዘመነ ዮሐንስ አደረሰዎ!! በማለት የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች መልካም ምኞታቸውን ይገልፃሉ፡፡ የትውፊቱ ባለቤትም ስለሆነች፡፡

እኛም ከወዲሁ እንኳን ከዘመን ዘመን አሸጋገርዎ! በማለት ለውድ አንባቢዎቻችን ይድረስ ብለናል፡፡ የዘመን መለወጫ እለት መስከረም አንድን/1/ እንቁጣጣሽ በመባል ትወደሳለች፡፡

በከሳቴ ብርሃን ተሠማ የአማርኛ መዝገበ ቃላት ትርጓሜ መሠረት እንቁጣጣሽ ማለት በክረምት ወቅት የሚበቅል እንግጫ ማለት ነው፡፡

ዘመን ተጠናቆ አዲስ ዘመን ሲበስር እለቱ ዓውደ ዓመት አዲስ ዘመን እና እንቁጣጣሽ እየተባለ ይጠራል፡፡

የቤተክርስቲያን ሊቃውነት እንቁጣጣሽ የሚለውን ስያሜ ኖኀ አህጉራትን ለሶስት ልጆቹ በእጣ ሲያከፋፍላቸው የአፍሪካ አህጉር የደረሰው ለካም ነበር፡፡

ካም ወደ አፍሪካ ምድር ሲገባም በመጀመሪያ ያረፈው በሃገራችን ኢትዮጵያ ነበር፡፡ ወደ ሃገሪቱ በገባም ጊዜ ምድሪቱ በአደይ አበባ አሸብርቃ ስላገኛት ወሯም መስከረም በመሆኗ ተደስቶ እንቁጣጣሽ ወጣልኝ በማለት ይህቺን ወቅት እንቁጣጣሽ ብሏታል ተብሎ ይነገራልም።

እንዲሁም ንግስት ሳባ የንጉስ ሰለሞንን ዜና ጥበብ እየሰማች ታደንቀ ነበር። እናም በጆሮዋ የሰማችውንም በዓይኗ ተመልክታ በማድነቅ በግመሎች ላይ ሽቶና እጅግ ብዙ ወርቅ በኢትዮጵያ ብቻ የሚገኝ በእየሩሳሌም የማይገኝ ልዩ ልዩ ገፀበረከት አስጭና ከብዙ ሠራዊት ጋር ወደ ኢየሩሳሌም አመራች፡፡

ከንጉስ ሰለሞን ጋር ተገናኝታ የያዘችውን ገፀ በረከት ከሰጠችው በኋላ በርካታ ነገሮችን ጠየቀችው፡፡ እርሱም አንድ ነገር ብቻ ሰውሮ ሁሉንም ነገር ገለፀላት፡፡ በቤተ መንግስቱ የሚገኙ እጅግ በጣም የከበሩ እንቁዎችን አስጐብኝቷት እንዳበቃ “እንቁ ለጣትሽ ጌጥ ይሁንልሽ” ሲል የከበረውን እንቁ አበረከተላት። ወሩም ወርሃ መስከረም ስለነበር ከዚህም በመነሳት አሁን የሚከበረውን የአከባበር ሥርዓት ይዞ እንደሚገኝ ድርሣነ ትውፊቶቻችን ጠቅሰውልናል፡፡

“እንቁ” እና “ጣጣሽ” የተሰኙት የሁለት ቃላት ጥምረት ሲሆኑ በየዓመቱ እንቁጣጣሽ ማለታችን የእንቁጣጣሽ ግብር /የእንቁጣጣሽ ገፀ በረከት/ ነው በማለት ለመመሰጋገንና መልካም ምኞታችንንም ለመለዋወጥ የምንጠቀምበት ስለመሆኑ ይነገራል፡፡

የኢትዮጵያ የዘመን መለወጫ መስከረም አንድ ቀን የሆነበትን ምክንያት ሊቃውንቱ ሲያስረዱ /ፀሐይ፣ ጨረቃና ከዋክብት/ የዓመቱን ኡደታቸውን በወርሃ ጳጉሜ አጠናቀው በመስከረም ወር ዳግመኛ ሲጀምሩ በመሆኑ ነው ይሉናል፡፡ በዚህም ጊዜ ሌቱ ከቀኑ ጋር እኩል ይሆናል በማለት ይገልፃሉ፡፡

ለዘመን መታወቂያ ይሆን ዘንድ ፀሐይን፣ ጨረቃንና ከዋክብትንም ፈጠረ እንዲል መፅሐፍ ቅዱስ /መ.ሄኖር 2፡1-49/

የመስከረም ወር ቀንና ሌቱ እኩል 12 ሠዓት የሚሆንበት ወቅት ይኸው ወር ነው፡፡ ምክንያቱም ከመስከረም 6 ቀን እስከ ታህሳስ 26 ቀን ድረስ ፀሐይ በምድር ወገብ አካባቢ ስለምትሆን ነው፡፡ ከዚህም በላይ ኖኀ እና ቤተሰቡ ከጥፋት ውሃ ድነው ምድር መድረቋን አበባና ፍሬ መስጠቷን የተመለከቱት በዚህ ወርሃ መስከረም ነበር /ዘፍ 8፡8/

በየዓመቱም /ከ12 ወራት በኋላ/ የዘመን መባቻ የመጀመሪያ ወይንም የዘመን መለወጫ አድርጐ ማክበሩም ይነገራል፡፡ እንዲሁም በዚሁ የመጀመሪያ ወር መባቻ ለራሱ መርከብ ይሠራ ዘንድ ታዘዘ፡፡ አበባ ማበብ ስትጀምርም የዘመን መለወጫ በወርሃ መስከረም ሆኖ ዛሬም እናከብራለን፡፡

በተጨማሪም ከጨለማ /የክረምት ወራት ወደ ብርሃን መሸጋገራችንን በማስመልከት ምሳሌያዊ አድርገንም የዘመን መለወጫችንን ከዚህ ጋር በማያያዝ መስከረም አንድን እንቁጣጣሽ ስንልም እንጠራለን ፤ እናከብራለን፡፡

እናም በወርሃ መስከረም ዋዜማና መባቻ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የአካባቢውን ወግና ባህል ተንተርሶ የክብረ በዓሉ ታዳሚ በመሆን በቀጥታና በተዘዋዋሪ እንደሚሳተፍ ልብ ማለታችን አልቀረም፡፡

የሀገራችን ብርቱ ደራሲና ጋዜጠኛ ካሳተሙልን የህብረ ብዕር መጽሃፍት ዋቢ የሆኑኝን ካህሳይ ገ/እግዚያብሔርን በአንባቢያንና በዝግጅቱ ክፍላችን ስም እነሆ ክብር ይድረስ ብዬአለሁ፡፡

መስከረም ዓውደ ዓመት፣ የክረምት ጫፉ መካተቻ የመፀው መባቻ ማለት ይሆናል ሲሉ መስከረም ለዓለም ሁሉ የመጀመሪያ ወር እንደሆነም ይታመናል ይላሉ ፀሐፊው፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የአቡሻኸር /ሥነ ፈለክ/ ሊቃውንት እግዚአብሔር ዓለምን የፈጠረው መስከረም 1 ቀን እንደነበር ይገልፃሉ፡፡

አባባላቸውንም በስሌት ጭምር አስደግፈው ያስረዳሉ፡፡ የመስከረም ወር በክረምት ወቅት የሚካተት ቢሆንም የጨለማው ጊዜ አልፎ ብርሃን የሚታይበት እፅዋትና አዝዕርት የሚያብቡበትና የሚያፈሩበት፣ እንስሳት የጠራ ውሃ የሚጠጡበትና ለምለም ሣር እየነጩ የሚቦርቁበት በአጠቃላይ ምድር በአበቦች የደመናው ብሉኮ /ጋቢውን/ ጥሎ ቀን ብቻ ሳይሆን ሌቱም በከዋክብት ማጌጥ የሚጀምርበት ወቅት ስለመሆኑ ፀሐፊው አትቶታል፡፡

የተለያዩ ወገኖችና ሊቃውንት የተለያዩ አስተያየቶችን ይሰነዝራሉ በማለት የመጀመሪያው መስከረም 1 ቀን ጥንት መሠረት ያለው በዓል እንጂ ከጊዜ በኋላ የተጀመረ በዓል አይደለም የሚል አስተሳሰብ ሲሆን ይህን ሐሳብ የሚያራምዱ ወገኖችም፡-

መስከረም 1 ቀን እግዚያብሔር መሬትን የፈጠረባትና ብርሃንንም ይሁን ብሎ ያወጀበት እለት መሆኑን ይገልፃሉ። ከዚህም በላይ ኖህ ከጥፋት ውሃ በኋላ የነበረባት መርከብ አራራት ተራራ ላይ ያረፈችበትና የጥፋት ውሃ ከመሬት መሸሹን ለማረጋገጥ የላካት እርግብ የወይራ ቅጠል ይዛ የተመለሰችበት እለት በመሆንዎ መስከረም 1 ቀን በዓውደ ዓመትነት መከበር ከኖኀ ጊዜ ጀምሮ ነውም ይላሉ ካህሣይ ገ/እግዚአብሔር፡፡ ሰናይ አዲስ ዘመን ይሁንልን!! ቸር እንሰንብት!