የስኳር በሽታን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚቻል ተገለፀ
የስኳር በሽታን ቀድሞ በመከላከልና በተገቢው ሕክምና መቆጣጠር እንደሚቻል በካፋ ዞን የገብረጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል አስገነዘበ።
በኢትዮጵያ የስኳር ህሙማን ማህበር የቦንጋ ቅርንጫፍ ዓለም አቀፍ የስኳር ሕመም ቀንን አስመልክቶ የሕዝብ ግንዛቤ ማሳደጊያና ነፃ ምርመራ መርሐ ግብር በቦንጋ ከተማ እያካሄደ ነው።
በመርሐ ግብሩ የስኳር በሽታን መከላከል፣ ቀድሞ ማወቅና በተገቢው ሕክምና መቆጣጠር ላይ ያተኮሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርቶች፣ አካላዊ እንቅስቃሴዎችና ነፃ የጤና ምርመራ አገልግሎቶች እየተሰጡ ይገኛል።
በገብረጻድቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል የውስጥ ደዌ ስፔሻሊስት የሆኑት ዶ/ር ሽመልስ አሪቶ እንዳሉት፤ የስኳር በሽታ በደም ውስጥ የሚገኝ የስኳር መጠን ከመደበኛው በላይ ሲሆን የሚከሰት ሥር የሰደደ የጤና ችግር ነው።
ዶክተር ሽመልስ አያይዘውም ሰውነት በቂ ኢንሱሊን ማምረት ሳይችል ሲቀር ወይም የሚያመርተውን ኢንሱሊን በትክክል መጠቀም ሳይችል ሲቀር የሚከሰት የጤና እክል መሆኑን አስረድተዋል።
ለበሽታው መከሰት ከሚያጋልጡ ሁኔታዎች መካከል የዘረመል ተጽዕኖ፣ ከመጠን በላይ ክብደት፣ የአካል እንቅስቃሴ አለማድረግ፣ ያልተመጣጠነ አመጋገብና ዕድሜ የመሳሰሉት ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
በተለይም በስኳር የበለጸጉ መጠጦችንና ከፍተኛ ካሎሪ ያላቸውን ምግቦች ከመጠን በላይ መጠቀም ለበሽታው የመጋለጥ ዕድልን እንደሚጨምር ጠቁመዋል።
በተደጋጋሚ መጠማት፣ ብዙ ሽንት መሽናት፣ ከመጠን በላይ የርሃብ ስሜት፣ ያለ ምክንያት ክብደት መቀነስ፣ ድካምና የዓይን ብዥታ የመሳሰሉት ከበሽታው ምልክቶች መካከል ተጠቃሽ መሆናቸውን ገልፀው፤ በመጀመሪያ ደረጃ ግልጽ ምልክት ላያሳይ ስለሚችል በየጊዜው የደም ስኳር ምርመራ ማድረግ ወሳኝ መሆኑን መክረዋል።
በኢትዮጵያ የስኳር ህሙማን ማህበር የቦንጋ ቅርንጫፍ የደም ስኳር ምርመራ ባለሙያ ወ/ሮ ቅድስት ተክሌ በበኩላቸው፤ በተገቢው ሕክምናና ቀጣይነት ባለው ክትትል የስኳር በሽታን መቆጣጠርና ከበሽታው ጋር ጤናማ ሕይወት መምራት እንደሚቻል ተናግረዋል።
ማህበሩ እንደ ታካሚው ሁኔታ በባለሙያ የታዘዘ የኢንሱሊን ሕክምና፣ የስኳር መቆጣጠሪያ መድኃኒቶች እንዲያገኙና የአመጋገብ ሁኔታን እንዲያስተካክሉ ማድረግ ጨምሮ ዘወትር የአካል እንቅስቃሴ እንዲያደርጉ የማስተማር አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በማህበሩ ሲገለገሉ አግኝተን ካነጋገርናቸው ተጠቃሚዎች መካከል ወ/ሮ አልማ ሀይለማሪያም እና አቶ ታምሩ ማሞ በሰጡት አስተያየት የተሻለ አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን ገልጸዋል።
ታካሚዎቹ በደም ስኳር ምርመራ ህመሙ ከተገኘባቸው ከ2 እስከ 10 ዓመት እንደሆናቸው ተናግረው፤ ማህበሩ ከነፃ ምርመራ ጀምሮ የተለያዩ አገልግሎቶች እንዲያገኙ እያገዘ በመሆኑ ተጠናክሮ እንዲቀጥል የባለድርሻ አካላት ትኩረትና እገዛ ያስፈልጋል ብለዋል።
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ የስኳር ህመም ቀን “ስኳር ህመም ላይ ቀድመን እርምጃ እንውሰድ” በሚል መሪ ቃል ከህዳር 5 ቀን 2019 ጀምሮ በተለያዩ ዝግጅቶች እየተከበረ መሆኑን የማህበሩ ሰብሳቢ አቶ አሸብር ኃይሌ ተናግረዋል።
በማህበሩ የቦንጋ ቅርንጫፍም ይህንኑ መርሀ ግብር ከህዳር 17-18/ 2019 በአካል እንቅስቃሴ፣ ነፃ የደም ስኳር ምርመራና የግንዛቤ ትምህርት በመስጠት እያከበረ መሆኑን ገልጸው፤ ማንኛውም ሰው በገብረጻዲቅ ሻዎ አጠቃላይ ሆስፒታል ግቢ እና በቦንጋ ከተማ መሀል አደባባይ በሚደረገው ነፃ ምርመራ በመሳተፍ ስለጤናው በማወቅ ከድንገተኛ የስኳር ህመም አደጋ ራሳቸውን እንዲጠብቁ ጥሪ አቅርበዋል።
ዘጋቢ፡ አሳምነው አትርሳው – ከቦንጋ ማስተባበሪያ

More Stories
በተሰጠው የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ከ474 ሺህ በላይ ህፃናት ክትባት ማግኘታቸውን የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ