የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት የነዳጅ ጥገኝነትን ለመቀነስና የአካባቢ ብክለትን ለመከላከል ጉልህ ፋይዳ እንዳለው ተገለጸ
በቤንች ሸኮ ዞን ሚዛን አማን ከተማ የአሃድ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን በይፋ ወደ ሥራ ለማስገባት የተዘጋጀ የትውውቅ መድረክ ተካሂዷል።
በመድረኩ ላይ የተገኙት የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ አሰገደች ወልደየስ፣ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መስፋፋት ሀገሪቱን ከነዳጅ ጥገኝነት ከማላቀቅና የካርቦን ልቀትን ከመቀነስ ባለፈ ለወጣቶች የሥራ ዕድል በመፍጠር የአካባቢውን ኢኮኖሚ እንደሚያነቃቃ ገልጸው፤ ክልሉም ለዘርፉ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።
የቤንች ሸኮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ተወካይ አቶ እሸቱ ሻምበል በበኩላቸው፣ የኤሌክትሪክ ባጃጆችና ሞተር ሳይክሎች ወደ ዞኑ መግባት በነዳጅ ዋጋ መጨመርና እጥረት ምክንያት በኅብረተሰቡ ላይ የሚደርሰውን ኢኮኖሚያዊ ጫና ለማረጋጋት ትልቅ ዕገዛ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።
አቶ እሸቱ አክለው የዞኑ አስተዳደርም ኩባንያው በአካባቢው ውጤታማ ሥራ እንዲያከናውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልጸዋል።
የአሃድ ቢዝነስ ግሩፕ ምክትል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን በካሎ እና የአፍሪ እና ኒኦ ፓወር (Afri & Neo Power) መሥራች አቶ ኬለይ ቼን፣ ድርጅቶቻቸው በሀገር አቀፍ ደረጃ ከ600 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ጠቁመው፤ በቀጣይም በሀገር ውስጥ የመገጣጠም ሥራንና የቴክኖሎጂ ሽግግርን በስፋት ተደራሽ ለማድረግ እንደሚሠሩ ተናግረዋል፡፡
በሚዛን አማን ከተማ የአሃድ ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዋና ወኪል አከፋፋይ አቶ መሐመድ ከድር፣ አገልግሎቱን ለማስፋፋት የመሥሪያና የማሳያ ቦታ እንዲመቻችላቸው የጠየቁ ሲሆን፣ የክልሉና የከተማው አመራሮችም ለጥያቄው አፋጣኝና በጎ ምላሽ ለመስጠት ዝግጁ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመርሐ-ግብሩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የኃይማኖት አባቶች እና የንግዱ ማኅበረሰብ ተወካዮች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ዮናስ ወ/ገብርኤል- ከሚዛን ቅርንጫፍ

More Stories
የትምህርት ብክነትን ለመቀነስ የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ
ለሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የካንጋሮ እናት እንክብካቤ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያግዝ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ
በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የጤና እክል የገጠማቸውን አካል ጉዳተኛ ህጻናት እና አሳዳጊ ወላጆችን የመደገፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት ገለፀ