የትምህርት ብክነትን ለመቀነስ የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ

‎የትምህርት ብክነትን ለመቀነስ የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ እንደሚገባ ተገለጸ
‎
‎በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽህፈት ቤት የማህበረሰብ መር የተማሪዎች ምገባ ማስጀመሪያ መርሃ ግብር ተካሂዷል።
‎
‎በከተማው አስተዳደር በክቢቻ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት በተካሄደው በማስጀመሪያ መርሃ ግብር በመገኘት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የጌዴኦ ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ ወይዘሮ እቴነሽ በየነ፣ መንግሥት በአቅም ውስንነት ምክንያት የሚባክነውን ትምህርት ለመቀነስ ሰፊ ስራ ሲሰራ መቆየቱን ጠቅሰው፤ የትምህርት ብክነትን ለመቀነስ የማህበረሰብ ተሳትፎን ማሳደግ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
‎
‎የተጀመረው የምገባ መርሀ ግብር ቀጣይነት እንዲኖረው የሁሉንም አካላት የነቃ ተሳትፎ እንደሚጠይቅና ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
‎
‎የጌዴኦ ዞን ትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ክብረወሰን  ተፈራ በበኩላቸው የተማሪዎችን ውጤት ለማሻሻል ትኩረት ሰጥተው እየሰሩ እንደሚገኙ አስታውሰው፤ በትምህርት ቤቱ የትምህርትን ብክነት ለመቀነስ የተጀመረውን ማህበረሰብ መር የተማሪዎችን ምገባ ወደ ሌሎችም ለማስፋፋት እንደሚሰራም አስገንዝበዋል።
‎
‎የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መንግሥቱ ተክሌ የተማሪዎችን ውጤት ማሻሻል በአንድ ጀንበር የሚሳካ ጉዳይ ባለመሆኑ እየተከናወነ ያለውን ጅምር ሥራዎችን በማስቀጠል የሚፈለገው ለውጥ እንዲመጣ ይሰራል ብለዋል።
‎
‎ትምህርት ቤቱ በከተማው ካሉት ትምህርት ቤቶች የተሻለ ውጤት ያስመዘገበ እንደሆነ  የተገለጸ ሲሆን ከቅድመ መደበኛ እስከ ስድስተኛ ክፍል 5 መቶ ለሚሆኑት ተማሪዎች  የማህበረሰብ መር የተማሪዎች ምገባ መጀመሩ ተመላክቷል።
‎
‎
‎ዘጋቢ: አማኑኤል ትዕግሥቱ- ከይርጋጨፌ ጣቢያችን