በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ

የክትባት ዘመቻው ከ33 ሺህ 150 በላይ ለሚሆኑ ህጻናት ተደራሽ እንደሚሆን ተመላክቷል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አባተ አበራ፤ ወላጆች ልጆቻቸውን የፖሊዮ ክትባት በማስከተብ ከልጅነት ልምሻ ለመከላከል ግዴታቸውን መወጣት እንዳለባቸው አሳስበዋል።

ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህፃናት ለበሽታው ይበልጥ ተጋላጭ የመሆን ዕድላቸው ሰፊ በመሆኑ ይህንን አስቀድሞ ለመከላከል የሁሉም ባለድርሻ አካላት ትብብር አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በማስጀመሪያ መርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ የህክምና አገልግሎቶች አስተባባሪ አቶ ደርጌቾ አህመድ በበኩላቸው፤ መንግስት የዜጎችን ጤና ለማስጠበቅ እና ተላላፊ በሽታዎችን ለመከላከል በትኩረት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የክትባት ዘመቻው ህጻናትን ከፖሊዮ በሽታ ሙሉ በሙሉ ለመታደግ ያለመ ሲሆን በመላው ሀገሪቱ የሚገኙ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ህጻናትን ተደራሽ ለማድረግ መታቀዱን አመላክተዋል።

የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ጤና ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ አቶ ደሣለኝ መኖሬ፤ ክትባቱን የወሰደን ህፃን በእጁ ላይ ምልክት ማድረግ እንዲሁም ቤት ለቤት ክትባት በተሰጠባቸው ቤቶችም ምልክት ማድረግ አስፈላጊ ነው ሲሉ አስገንዝበዋል።

በመጀመሪያው ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ በልዩ ወረዳው ከ33 ሺህ 150 በላይ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት እንደሚከተቡ ተናግረዋል።

ክትባቱ ሕፃናትን ለፖሊዮ በሽታ ከመጋለጥ የሚያድን አስፈላጊ የጤና እንክብካቤ መሆኑን ያስታወሱት ምክትል ኃላፊው፤ ዘመቻው ይበልጥ ውጤታማ እንዲሆን ከሁሉም ባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት እየተሠራ እንደሆነም አብራርተዋል።

የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ለተከታታይ አራት ቀናት በልዩ ወረዳው በሚገኙ በሁሉም ቀበሌያት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።

ከክትባት ዘመቻ ጎን ለጎን የምግብ እጥረትና የፖሊዮ በሽታ ያለባቸውን ህፃናት የመለየትና ህክምና እንዲያገኙ የማድረግ እንዲሁም የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን ህፃናት የመለየት ስራ ጨምሮ በርካታ ስራዎች እየተሠሩ መሆናቸው ተመላክቷል።

በዘመቻው የታለመው ዓላማ እንዲሳካ ሁሉም የበኩሉን ኃላፊነት በተገቢው መወጣት እንዳለበት ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ:- ማቲዎስ ሀደሮ- ከሆሳዕና ጣቢያችን