ለሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የካንጋሮ እናት እንክብካቤ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያግዝ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

ለሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የካንጋሮ እናት እንክብካቤ አገልግሎትን ለማጠናከር የሚያግዝ የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ

በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በከምባታ ዞን ሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስቸኳይ የካንጋሮ እናት እንክብካቤ (IKMC) አገልግሎትን ለማጠናከር በኢንጀንደር ኸልዝ (Engender Helth) ዓለም አቀፍ የልማት ድርጅት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ ተደረገ።

የሲዳማ፣ የደቡብ ኢትዮጵያ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልሎች የኢንጀንደር ኸልዝ ቡድን መሪ  አቶ ተስፋዬ ኦርዶሎ ድጋፉ በተደረገበት ወቅት ባደረጉት ንግግር፤ የተደረገው ድጋፍ የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመቀነስ ሀገሪቱ ካስቀመጠችው ግብ አንጻር የጨቅላ ህጻናት ሞት ከ25 በመቶ ወደ 12 በመቶ ዝቅ ለማድረግ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።

አስቸኳይ የካንጋሮ እናት እንክብካቤ ማለት በተለይ ያለጊዜያቸው  ለተወለዱና ክብደታቸው ዝቅተኛ ለሆኑ ሕፃናት በእናት ወይም በአሳዳጊ ሰው የቆዳ ለቆዳ ንክኪ (skin-to-skin contact) እንክብካቤ የሚሰጥበት ዘዴ ነው ብለዋል።

ፕሮጀክቱ በሀገር አቀፍ ደረጃ በ6 ሆስፒታሎች እየተተገበረ እንደሚገኝ እና በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልልም ከሁለት ዓመታት በላይ ስራ ላይ መቆየቱን ገልጸው፤ ብዙ ወጪ የማይፈልጉ ነገር ግን ከፍተኛ የጤና ፋይዳ ያላቸው ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን አብራርተዋል።

አስቸኳይ የካንጋሮ እናት እንክብካቤ (IKMC) አገልግሎት እንደ ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላይ ብቻ መጀመሩን የገለጹት አቶ ተስፋዬ፤ ይህም ለተቋሙ ትልቅ እድል ከመፍጠሩም በላይ ለአካባቢው ጤና ተቋማት አገልግሎት ይሰጣል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተናግረዋል።

በከምባታ ዞን ሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አስቸኳይ የካንጋሮ እናት እንክብካቤ አገልግሎትን ለማጠናከር ድጋፍ በተደረገበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የዞኑ ጤና መምሪያ ኃላፊ አቶ ቻላቸው ዋንጎሬ በበኩላቸው፤ መሰል ሁነቶችን እንደ ዞን እንደ መልካም አጋጣሚ ልንጠቀም ይገባል ብለዋል።

በመንግሥት ፖሊሲ የእናቶች እና ህጻናት እንዲሁም ለወጣቶች ትልቅ ቦታ ተሰጥቶ ስራዎች እንደሚሰሩ ጠቁመው፤ የእናቶችን እና የጨቅላ ህጻናትን ሞት ለመከላከል የሚሰሩ ስራዎችን ለማጠናከር ኢንጀንደር ኸልዝ በሙሉ ፈቃደኝነት ላደረገው ድጋፍ አመስግነዋል።

እንደ ዞን በመተጋገዝ ከአጋሮችም ጋር በጋራ በመሆን እናቶችንና ህጻናትን ከሞት ለመታደግ እንሰራለን ብለዋል።

የህብረተሰቡን ጤና ለማሻሻል እንደ ሀገር ብሎም እንደ ክልል በርካታ የንቅናቄ ስራዎች እየተሰሩ ናቸው ያሉት ደግሞ የክልሉ ጤና ቢሮ የእናቶች እና ህጻናት ጤናና ስርዓተ ምግብ አገልግሎት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ተወካይ አቶ ተመስገን አብዲ ናቸው።

በፖሊሲ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ የሚገኘው የጨቅላ ህጻናት፣ የህጻናት እና የእናቶችን ህመም፣ እንግልት እንዲሁም ሞት ለመቀነስ እንደ ክልል በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ገልጸዋል።

በተለይ እናቶችን ለሞት የሚዳርጉ ከፍተኛ የደም መፍሰስ እና የደም ግፊት እንዲሁም ከወሊድ ጋር ተያይዘው የሚመጡ በርካታ ችግሮችን ለመቅረፍና የእናቶችን ሞት ለመከላከል በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

መንግስት ከሚሰራው ስራ በተጨማሪ ባለሀብቱን በማንቀሳቀስ እና ህብረተሰቡን በማሳተፍ የተለያዩ ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነ ያስታወሱት አቶ ተመስገን፤ መሰል ደጋፊ አካላትን በማስተባበር የማህበረሰቡን ጤና በጋራ ማሻሻል ያስፈልጋል በማለት ኢንጀንደር ኸልዝ በተለይም የእናቶችን እና የህጻናትን ሞት ለመቀነስ በሚሰራው ስራ በሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ላደረገው የቁሳቁስ ድጋፍ አመስግነዋል።

የሺንሺቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ማርቆስ ኢንጀንደር ኸልዝ ከዚህ ቀደምም ለባለሙያ የአቅም ግንባታ ስልጠና ከመስጠት አንስቶ የተለያዩ  የህክምና ቁሳቁስ ድጋፎችን እንዳደረገ አስታውሰው፤ ክብደታቸው ከ2 ሺህ 500 ግራም በታች ለሆኑ ጨቅላ ህጻናት ሙቀት የሚሰጥ የህክምና ማሽን እና የሆስፒታሉን አገልግሎት ለማዘመን የሚረዱ የኮምፒውተሮች ድጋፍ ማድረጉ እንዳስደሰታቸው በመግለጽ አመስግነዋል።


በመጨረሻም በሆስፒታሉ የፕሮጀክቱ አፈጻጸም ሪፖርት ለባለድርሻ አካላትና ለሆስፒታሉ ሠራተኞች የቀረበ ሲሆን በተጨማሪም የጨቅላ ሕፃናት ሕክምና አገልግሎት ተጎብኝቶ የቁሳቁስ ርክክብ ተደርጓል።



ዘጋቢ:- ኤደን ተረፈ ከሆሳዕና  ጣቢያችን