የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ‎በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ

የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ‎በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ

የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር ‎በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ

‎የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ- ግብር በበና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ አካሂዷል።
‎
የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ-ግብሩ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ተወካይ አቶ አጉኔ አሾሌ፣ በክልሉ በሁሉም ዞኖች ለአራት ተከታታይ ቀናት ከአምስት ዓመት በታች ለሆኑ ህፃናት ቤት ለቤት ክትባቱ በዘመቻ እንደሚሰጥ ገልፀው፤ እንደ ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ1.5 ሚሊየን በላይ የሚሆኑ ህፃናት ክትባቱን እንደሚወስዱ ጠቁመዋል።
‎
‎የደቡብ ኦሞ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋ ዳምጠው በበኩላቸው፣ በዞኑ ስድስት ወረዳዎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች በተቀናጀ መልኩ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው እንደሚከናወን ገልጸው፤ በዞኑ ከ108 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህፃናት የልጅነት ልምሻ ክትባቱን እንደሚወስዱ አስረድተዋል።
‎
‎ቤት ለቤት በሚካሄደው በዚሁ መርሐ-ግብር በተጓዳኝ እግራቸው ቆልማማ ሆነው የተወለዱ ህፃናትን፣ የማህፀን ውልቃት ያለባቸው እናቶችን እንዲሁም የምግብ እጥረት ያለባቸው ህፃናትን የመለየት ሥራና የተሻለ ህክምና እንዲያገኙ ማድረግ ተቀዳሚ ሥራ መሆኑን አስታውሰው፤ በደቡብ ኦሞ ዞን ድንበር አካባቢ በኬኒያ የተከሰተው የኢቦላ ወረርሽኝ በዞኑ እንዳይከሰት የግንዛቤ ማስጨበጫና የልየታ ሥራዎች እንደሚካሄዱም አቶ ተስፋ አክለዋል።
‎
‎የበና ፀማይ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሐንሰ ጋርሾ፣ እንደ ወረዳ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀትና ቅድመ ዝግጅቶችን በማድረግ ወደ ተግባር መገባቱን ጠቅሰው፤ እንደ ወረዳ ከ22 ሺህ በላይ የሚሆኑ ህፃናት ክትባቱን ያገኛሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
‎
‎አስተያየታቸውን ከሰጡ እናቶች መካከል ወ/ሮ ሶይቲ አይኬ እና ወ/ሮ ጋባ ኡካ፣ ልጆቻቸው በፖሊዮና በተጓዳኝ በተለያዩ በሽታዎች እንዳይጠቁ በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት ልጆቻቸውን እያስከተቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል::
‎
‎በዞኑ የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻው በስኬት እንዲጠናቀቅ የተለያዩ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ድጋፍ ማድረጋቸውም ተገልጿል።
‎
‎ዘጋቢ፡- ግዳጁ ጎሮጊ- ከጂንካ ጣቢያችን