በተሰጠው የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ከ474 ሺህ በላይ ህፃናት ክትባት ማግኘታቸውን የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ አስታወቀ
በዘመልቻ መልክ ለ4 ተከታታይ ቀናት በተሰጠው የፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ከ474 ሺህ በላይ እድሜያቸው ከአምስት አመት በታች የሆኑ ህፃናት ክትባት ማግኘታቸውን የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ አስታውቋል።
የክትባት ዘመቻው በተሳካ መንገድ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላደረጉ አካላትም መምሪያው ምስጋና አቅርቧል።
የሀዲያ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ተወካይ እና የበሽታ መከላከልና ጤና ማጎልበት የስራ ሂደት አስተባባሪ አቶ ቸርነት ሰዎሬ እንደገለጹት፤ የክትባት ዘመቻው ከመጀመሩ አስቀድሞ በዞኑ በሁሉም መዋቅሮች የጤና ባለሙያዎችን ከማሰልጠን ጀምሮ በቂ ዝግጅት ማድረግ መቻሉን አስታውሰዋል።
በዞኑ በመጀመሪያ ዙሪ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ለ452 ሺህ 197 ሕፃናት ክትባት ለመሥጠት የታቀደ ቢሆንም ለ4 ተከታታይ ቀናት በተሰጠው የክትባት ዘመቻ 474 ሺህ 504 ህፃናት መከተባቸዉን አቶ ቸርነት ገልፀዋል።
የዘመቻ ስራው የተሳካ እንዲሆን እንደዞን 971 የጤና ቡድን አባላት በአምስት ምድብ ሆነዉ የክትትል ስራ እንዲሰሩ ማሰማራት መቻሉንም አንስተዋል።
ከፖሊዮ በሽታ መከላከያ ክትባት ጎን ለጎን ከ2 ሺህ በላይ መደበኛ ክትባት ያቋረጡ ህፃናትን ጨምሮ ዕድሜያቸው ከአንድ አመት በታች የሆኑና ክትባት ያልወሰዱ 300 ህፃናት በመገኘታቸዉ በጤና ተቋማት መደበኛ ክትባት እንዲከታተሉ መደረጉንም ገልጸዋል።
የፖሊዮ በሽታ ምልክት የታየባቸው 4 ሕፃናት፣ ቆልማማ እግር ያላቸውን 7 እንዲሁም የከንፈርና የላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን 8 ህጻናት የመለየት ሥራ መሰራቱንም አቶ ቸርነት ጠቅሰዋል።
በክትባት ዘመቻ ወቅት ከወሊድ እና ከተለያዩ ችግሮች ጋር በተያያዘ የማህፀን ችግር ያለባቸው 5 እናቶችን በመለየት በቀጣይ ተገቢውን ህክምና የሚያገኙበት ሁኔታ መመቻቸቱን አቶ ቸርነት አስረድተዋል።
በየቀኑ የተሰሩ ስራዎች እየተገመግሙ ችግሮች እንዲቀረፉ በመደረጉ የተሻለ ውጤት ተመዝግቧል ያሉት ተወካዩ፤ በተለያዩ ምክንያቶች ክትባቱን ያላገኙ ህጻናት አሁንም ወደ ጤና ተቋማት መጥተው ክትባቱን ማግኘት እንደሚገባቸውም አሳስበዋል።
የክትባት ዘመቻው በተሳካ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ያደረጉ የአስተዳደር አካላትን፣ የጤና ባለሙያዎችንና ሌሎች ባለድርሻ አካላትንም አቶ ቸርነት በመምሪያው ስም አመስግነዋል።
ዘጋቢ: ተሻለ ከበደ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የስኳር በሽታን ቀድሞ መከላከልና መቆጣጠር እንደሚቻል ተገለፀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠምባሮ ልዩ ወረዳ የመጀመሪያ ዙር የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት መሰጠት ተጀመረ
የተቀናጀ የፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ማስጀመሪያ መርሐ ግብር በደቡብ ኦሞ ዞን በና ፀማይ ወረዳ በአልዱባ ከተማ ተካሄደ