በሕፃናት ላይ የሚታየውን የከንፈርና ላንቃ ክፍተት ችግር ለመቅረፍ ተጨባጭ ተግባራት መከናወናቸውን የኢፌዴሪ ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ
በአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል የህፃናት ቀዶ ህክምና ክፍል የማስፋፊያ እና የማዘመን ስራ በይፋ ተመርቋል።
በሕፃናት ላይ የሚታየውን የከንፈርና ላንቃ ክፍተት ችግር ለመፍታት የሚደረጉ የሕክምና አገልግሎቶች የሕፃናትን ጤና፣ የንግግር ክህሎትና ማኅበራዊ ተሳትፎ ለማሻሻል ወሳኝ ሚና አላቸው።
በመርሀ ግብሩ ተገኝተው የእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ያደረጉት የአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ ዶክተር ምባቸው ዱማ፤ ሆስፒታሉ ለበርካታ አመታት ከረጂ ድርጅቶች ጋር በጋራ በመሆን የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ መስራቱንና በዚህም በርካታ ለውጦች መታየታቸውን ገልጸዋል።
ይህ የተቀደሰ ተግባር በህፃናት ጤና ላይ የሚስተዋለውን በማህበራዊ እና ስነልቦናዊ ችግሮች በመፍታት የወደፊት ህይወታቸውን የሚያለመልም በመሆኑ ስማይል ትሬን (Smaile train ) ላመሰግን እወዳለሁ ብለዋል።
የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ በበኩላቸው፤ በዞኑ የህፃናትን ጤና ለመጠበቅ ከሚከናወኑ ተግባራት ባሻገር የጤና ስራዎችን ተደራሽና ዘመናዊ ከማድረግ ባሻገር የሚስተዋሉ ክፍተቶችን ለመሙላት እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሊመሰገኑ ይገባል ሲሉ ገልጸዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ፤ የከንፈርና ላንቃ መሰንጠቅ ችግር ያለባቸውን ህፃናት ህይወት ብሩህ ለማድረግ ‘ስማይል ትሬን’ ባደረገው ድጋፍ በክልል አዲስ ተስፋና ፈውስ እንዲመዘገብ አዎንታዊ ሚና ተጫውቷል።
በህፃናትና በወላጆች ላይ ይደርስ የነበረውን ማህበራዊ እና ስነ ልቦናዊ ችግር በመቅረፍ አምራች ዜጋ ለመፍጠር የምናደርጋቸውን ጥረት ያገዘ ነው ሲሉ ረጋግጠዋል።
በኢፌዲሪ ጤና ሚኒስቴር የህክምና መሳሪያዎች አገልግሎት መሪ ስራ አስፈፃሚ ተወካይ አቶ ኤርሚያስ ሙላቱ፤ ኢትዮጵያ በሕፃናት ላይ የሚታየውን የከንፈርና ላንቃ ክፍተት ችግር ለመፍታት የተለያዩ የጤና ተቋማትና አጋር ድርጅቶች በትብብር እየሠሩ እንደሚገኙ ተናግረዋል።
መንግስት ቀድሞ የመከላከል ፖሊሲን ተግባራዊ በማድረጉ በዘርፉ መሻሻሎችን ማስመዝገቡን ያብራሩት አቶ ኤርሚያስ፤ በቀጣይም ማዕከሉን ከመጠበቅ ባሻገር የተሻለ አገልግሎት እንዲሰጥ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ መስራት እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በምረቃው መርሀ ግብር የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የጤና ፕሮግራም ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ፣ የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ፣ የአርባምንጭ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ትብብር ምክትል ፕሬዝዳንት ተክሉ ወጋዬሁ (ዶ/ር)፤ የስማይል ትሬን ከፍተኛ አመራሮች፣ የአርባምንጭ አጠቃላይ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ ዶክተር አምባቸው ዱማ፣ የአርባምንጭ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል ኤክስኪዩቲቭ ዳይሬክተር ዶክተር ደስታ ጋልቻን ጨምሮ የሆስፒታሉ የማኔጅመንት አባላት ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ተመኙህ ገረሱ – ከአርባምንጭ ጣቢያችን

More Stories
የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ
ሆስፒታሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እንዳዳናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዜጎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ የሚጠብቅ አገልግሎት መሆኑ ተገለጸ