ሆስፒታሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እንዳዳናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ

ሆስፒታሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እንዳዳናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ

በኮንታ ዞን አማያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እንዳዳናቸው ተገልጋዮች ገለጹ።

የአማያ ዙሪያ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ወ/ሮ ታደለች ገብሬ እንደተናገሩት፤ በዓመት 1 ሺህ 600 ብር በከፈሉት የጤና መድህን መዋጮ ያጋጠማቸውን የአንገትና የራስ ምታት ህክምናቸውን በነፃ መከታተል መቻላቸውን ገልፀው፤ ቤተሰባቸውም በቂ የመድኃኒትና የሕክምና አገልግሎት ከአመያ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል እንዲያገኙ እንዳስቻላቸው ተናግረዋል።

ከካፋ ዞን ምንጃ ወረዳ የመጡት አቶ አየለ አንጎ በበኩላቸው፤ ባለቤታቸው በጤና መድህኑ አማካኝነት የነፃ ቀዶ ህክምና (ኦፕሬሽን) አግኝተው መዳናቸውንና ለሁለተኛው ቀዶ ህክምና ቀጠሮ እየተከታተሉ እንደሚገኙ ገልጸዋል።

ጤና መድህን ባይኖር ለቀዶ ህክምና፣ ለአልጋና ለመድኃኒት ከ50 ሺህ ብር በላይ ይወጣ እንደነበር የጠቆሙት አቶ አየለ፤ ሰባት የቤተሰባቸው አባላት አንድ ጊዜ በከፈሉት የማኅበረሰብ አቀፍ የጤና መድን ክፍያ በመታገዝ የሕክምና አገልግሎት እያገኙ መሆናቸውን አስረድተዋል።

የፋርማሲ ባለሙያ የሆኑት አቶ ብርሃኑ በየነ በበኩላቸው፤ የመድኃኒት አቅርቦቱ ከጤና መድህኑ መጀመር በኋላ 80 በመቶ ማደጉን ገልፀው፤ ክፍተቶች ሲፈጠሩ በፕሮግራም እና በድንገተኛ ግዢ እንደሚሟሉ ጠቅሰዋል።

ከአንድ ወር በፊት ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ከ2 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ መድኃኒቶች ተገዝተው ለህብረተሰቡ አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ አብራርተዋል።

የአማያ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ አለማየሁ አሻ በበኩላቸው፤ ሆስፒታሉ የኮንታ ዞን ሙሉ ህዝብ እንዲሁም ከአጎራባች ካፋ ዞን፣ ዳውሮ እና ኦሮሚያ ክልሎች የሚመጡ ታካሚዎችን እያገለገለ ይገኛል ብለዋል።

ሆስፒታሉ 75 የጤና ባለሙያዎች ያለው ሲሆን፣ 85 ከመቶ በላይ የሚሆኑ ታካሚዎች በጤና መድህን ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸው፤ ዞኑ ባወጣው 6 ሚሊዮን ብር የካርድ እና ክፍያ አገልግሎቶችን በአንድ ቦታ በማደራጀት እንግልት እንዲቀነስ መደረጉን ተናግረዋል።

የመድኃኒት አቅርቦቱን አስተማማኝ ለማድረግ በአዲሱ በጀት ዓመት 16 ሚሊዮን ብር ለመድኃኒት እና 6 ሚሊዮን ብር ለላቦራቶሪ ሪኤጀንቶች ከኢትዮጵያ መድኃኒት አቅርቦት አገልግሎት ጋር ውል ተግበቶ በመሰራቱ የመድኃኒት እጥረት ለመቅረፍ እየተሰራ እንዳለም ጠቁመዋል፡፡

የኮንታ ዞን ጤና መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አስተባባሪ አቶ ሰጉዴ ኮርቾ እንደገለጹት፤ በ2011 ዓ.ም በ2 ሺህ አባላት የተጀመረው የጤና መድህን አገልግሎት በአሁኑ ወቅት 19 ሺህ 673 አባላት ያሉት ሲሆን በአዲሱ በጀት ዓመት ቁጥሩን ወደ 23 ሺህ 600 ለማድረስ ዝግጅት መደረጉን ገልጸዋል።

የጤና ተቋማት የመድኃኒት አቅርቦታቸው እንዳይስተጓጎል የ6 ወር ቅድመ ቁርጥ ክፍያ (Capitation) በልዩ አካውንታቸው ገቢ እንደሚደረግ እና አሰራሩን ዘመናዊ ለማድረግ አባላትን “ከፋይዳ” (Fayda) ብሔራዊ መታወቂያ ጋር የማገናኘትና አገልግሎቱን ዲጂታላይዝ ለማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

የጤና መድህን መዋጮ ነባርና አዲስ አባላት እድሳትና ምዝገባ ከህዳር እስከ ታህሳስ 30 ቀን 2019 ዓ.ም ድረስ እንድሚቆይ አቶ ሰጉዴ ጠቁመዋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድርሻዬ ጋሻው – ከዋካ ጣቢያችን