የሃይማኖት ተቋማት ዜጎች በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን የማሻሻል እና ሌሎችን የማገልገል የሞራል ግዴታን በማስተማር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

የሃይማኖት ተቋማት ዜጎች በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን የማሻሻል እና ሌሎችን የማገልገል የሞራል ግዴታን በማስተማር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑ ተገለፀ

የሃይማኖት ተቋማት ዜጎች በራሳቸው ጥረት ኑሯቸውን የማሻሻል እና ሌሎችን የማገልገል የሞራል ግዴታን በማስተማር ረገድ ሚናቸው የጎላ መሆኑን የጉራጌ ዞን አስተዳደር ገልጿል።

የኢትዮጵያ ኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ዓለም አቀፍ የሥራ ፈጠራ ሳምንት “ምቹ ሥነ-ምህዳር ለኢንተርፕረነሮች ስኬት!” በሚል መሪ ቃል ከሃይማኖት አባቶችና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በወልቂጤ ከተማ አክብሯል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በመክፈቻ ንግግራቸው፤ በዚህ ሳምንት በመላው ዓለም ወደ 200 በሚጠጉ ሀገራት የስራ ፈጠራ ሳምንት እንደሚከበር ጠቁመው፤ በክልሉ ብሎም በዞኑ ትርጉም ባለው መንገድ መንፈሳዊ አባቶች እና የሥራ ፈጠራ ባለድርሻ አካላትን በማገናኘት ማክበር መቻሉን ተናግረዋል።

ሁሉም የሃይማኖት አስተምህሮቶች ስለ ሥራ ክብር፣ በራስ ጥረት ስለመኖር እና ሌሎችን የማገልገል የሞራል ግዴታን እንደሚያስተምሩ ጠቅሰው፤ በሥራ ፈጠራ ትርፍ ማግኘት ብቻ ሳይሆን በዋናነት ችግሮችን መፍታት፣ ለሌሎች የሥራ ዕድል በመፍጠር ቤተሰቦቻችንን እና አካባቢያችንን ከድህነት ማውጣት ነው ሲሉ አቶ አበራ ገልጸዋል፡፡

የሃይማኖት አባቶች በማህበረሰቡ ውስጥ ተሰሚነት ስላላቸው ምክራቸው አስተሳሰብንና ሥነ-ምግባርን እንደሚቀርፅ ገልፀዋል።

አያይዘውም ወጣቶች ሥራ ፈላጊዎች ብቻ ሳይሆኑ ሥራ ፈጣሪዎች መሆን የሚችሉበት የፈጠራ ችሎታ እና አቅም እንዳላቸው በማሳመን ወደ ተግባር መቀየር እንዲችሉ ቅንጅታዊ ስራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የኢንተርፕረነርሺፕ ልማት ኢንስቲትዩት ኢዲአይ አሰልጣኝ እና የቢዝነስ አማካሪ አቶ ሀፍቶም ወልደሩፋኤል በበኩላቸው፤ ኢንስቲትዩቱ ከ18 እስከ 35 ዓመት ዕድሜ ክልል ውስጥ ለሚገኙ ወጣቶች የስራ ፈጠራ ስልጠና፣ የቢዝነስ ማማከር፣ የብድር አገልግሎት እና የገበያ ትስስር በማመቻቸት ላይ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ኃላፊው አክለውም ኢንስቲትዩቱ ተቋማት ከተለምዷዊ አሰራር በተለየ መንገድ እንዲሰሩ የሚያስችል ስልጠና እየሰጠ መሆኑን ገልፀው፤ የሥራ ፈጠራና የኢኖቬሽን ሥነ-ምህዳር ዋነኛ ተዋናይ ሆኖም እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

በዓለም አቀፍ የስራ ፈጠራ ሳምንት ማዕቀፍ የተዘጋጀው ይህ መድረክ ወጣቶች ከአካባቢያቸው ፀጋ በመነሳት ችግር ፈቺ የቢዝነስ ሀሳቦችን እንዲያዳብሩ፣ ግብ እንዲኖራቸው እና በጽናት እንዲሰሩ ለማነሳሳት ያለመ እንደሆነ አቶ ሃፍቶም አስረድተዋል።

የሃይማኖት ተቋማት ወጣቶችን በስነ-ምግባር በመቅረፅ ጠንካራ የሞራል ስብዕና እንዲኖራቸው በማድረግ ንግዳቸውን በታማኝነት፣ በፍትሃዊነት እና በርህራሄ መስራት እንዲችሉ የሚጫወቱት ሚና የጎላ መሆኑን አብራርተዋል።

የኢዲአይ ስራዎች ውጤታማ እንዲሆኑ ከክልል አመራሮች እና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተቋማዊ አጋርነት መፍጠር አስፈላጊ መሆኑን በመጠቆም የትብብር ጥሪ አቅረበዋል።

የጉራጌ ዞን ስራና ክህሎት መምሪያ ምክትልና እና የክህሎት ዘርፍ ኃላፊ ወ/ሮ ጠጄ ደነቀ እንደገለፁት፤ የስራና ክህሎት ከተለመደው አሰራር በመውጣት ጊዜው የሚፈቅደው ስልጠና ከመስጠት ባሻገር ለጀማሪ ስራ ፈጣሪዎች የብድር፣ የመስሪያና መሸጫ ቦታ እንደሚመቻች ተናግረዋል።

በአሁኑ ወቅት በቴክኒክና ሙያ ተቋማት ላይ ያለው የግንዛቤና የአመለካከት ውስንነት በመቀየር ዜጎች በነዚህ ተቋማት እንዲሰለጥኑ ሁሉም ኃላፊነቱን እንዲወጣ ወ/ሮ ጠጄ አሳስበዋል።

የመድረኩ ተሳታፊ የሃይማኖት አባቶች በበኩላቸው፤ ሁሉም የሃይማኖት ተቋማት ለምዕመኑ ከጠባቂነት ይልቅ በራስ ላብ ሰርቶ መብላትን እንደሚያስተምሩ ገልፀው፤ ጠንካራ የስራ ባህል በአስተምህሮታቸው እንደሚያበረታታም ተናግረዋል።

ተቋማቱ ለእምነቱ ተከታዮች መንፈሳዊ ትምህርት ከማስተማር ባሻገር በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ የስራ እድል የማመቻቸት እሳቤ ማዳበር እንደሚገባ ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ፍስሃ ክፍሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን