የፖሊዮ በሽታን ለመከላከል በሚሰጠው የክትባት ዘመቻ ውጤታማ እንዲሆን የማህበረሰቡን ተሳትፎ ማጠናከር እንደሚገባ ጥሪ ቀረበ
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ጋር በመተባበር በፖሊዮ ክትባት ዘመቻ ዙሪያ ለሃይማኖት መሪዎች፣ ለሚዲያና ለመንግሥት ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ ወ/ሮ አሚናት ሰይድ በክትባት ዘመቻው ቀደም ሲል የመደበኛ ክትባት መርሐ ግብር የወሰዱም ሆነ ያልወሰዱ ዕድሜያቸው ከአምስት ዓመት በታች የሆኑ ሕፃናት ሁሉ በዘመቻው እንዲከተቡ በትኩረት እንደሚሠራ ገልጸዋል።
ፖሊዮ በተለይ በሕፃናት ላይ ከባድ የጤና ጉዳት ሊያደርስ የሚችል በሽታ በመሆኑ በክትባት ለመከላከል በሚደረገው ጥረት ላይ የማኅበረሰቡ የጋራ ተሳትፎ ወሳኝ መሆኑን አመላክተዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ የጤና ኤክስቴንሽን ፕሮግራም አስተባባሪና የተግባቦት ባለሙያ አቶ ታደለ ዶይሎ፤ ለሐይማኖት መሪዎችና ለሚዲያ ባለሙያዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ሰነድ አቅርበው ውይይት ተደርጎበታል።
ሃይማኖት መሪዎች በማኅበረሰቡ ውስጥ ያላቸውን ተደማጭነት በመጠቀም ስለክትባቱ ጠቀሜታ ትክክለኛ መረጃ እንዲያስተላልፉ እና በክትባት ዙሪያ ሊኖሩ የሚችሉ የተሳሳቱ ግንዛቤዎችን በማረም ረገድ ንቁ ሚና እንዲወጡ የሚያስችል መሆኑን አብራርተዋል።
የሚዲያ ተቋማትም የሕዝቡን ግንዛቤን በማሳደግ፣ ስለክትባቱ አስፈላጊነት በተደራሽና ግልጽ ቋንቋ መረጃ በማቅረብ የዘመቻውን ዓላማ ለማሳካት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ትኩረት እንደተሠጠውም አቶ ታደለ አመላክተዋል።
የመንግሥት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ባለሙያዎችም ከጤና ተቋማትና ከሌሎች አጋር አካላት ጋር በመቀናጀት የመረጃ ስርጭቱን ማጠናከርና ማኅበረሰቡን ማንቀሳቀስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።
ተሳታፊ የሐይማኖት መሪዎችና የሚዲያ ባለሙያዎች በበኩላቸው ግልጸኝነት በሚፈልጉ ጉዳዮች ዙሪያ ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን በአጠቃላይ ዘመቻው የሚፈለገውን ውጤት እንዲያመጣ የበኩላቸውን እንደሚወጡ አረጋግጠዋል።
የዞኑ ጤና መምሪያ ምክትል ኃላፊ በሰጡት ማብራሪያ ከፖሊዮ ክትባት ዘመቻው ጎን ለጎን የእናቶችና የሕፃናት የአመጋገብ ሁኔታ ለመለየትና የምግብ እጥረት ሊኖርባቸው የሚችሉ ወገኖችን በመለየት ተገቢውን የጤና አገልግሎት እንዲያገኙ እንዲሁም ከኢቦላ ቫይረስ ጋር ተያይዘው ሊታዩ የሚችሉ ምልክቶችን በመከታተል አጠራጣሪ ሁኔታዎችን በጊዜ ለተገቢው የጤና አካል ሪፖርት ለማድረግ አስፈላጊው ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።
ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
ሆስፒታሉ የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን አገልግሎት መስጠት መጀመሩ ከከፍተኛ የህክምና ወጪ እንዳዳናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዜጎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ የሚጠብቅ አገልግሎት መሆኑ ተገለጸ
በሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት መዳናቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት በመጡበት ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ