ጋና ለዓለም ያበሰረችው ምንድነው?

ጋና ለዓለም ያበሰረችው ምንድነው?

ምዕራብ አፍሪካዊቷ ሀገር ከውሃ አካላት ከአትላንቲክ ውቅያኖስ ጋር ትዋሰናለች፡፡ ከሀገራት ደግሞ አይቮሪኮስት፣ ቡርኪናፋሶ እና ቶጎ በድንበር ያዋስኗታል፡፡ ከ35 ነጥብ 9 ሚሊየን በላይ የሕዝብ ብዛት አላት፡፡

239 ሺህ 567 ስኩዌር ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ትሸፍናለች፡፡ በፖለቲካው ረገድ አህዳዊ የመንግስት ስርዓት ትከተላለች፡፡ በአሁኑ ወቅት ሀገሪቱ ላይ ሥልጣን ተቆናጥጠው እየመሯት የሚገኙት ፕሬዝደንት ጆን ድራማኒ ማሃማ ናቸው፡፡

በምጣኔ ሃብት ረገድም በአህጉሪቱ መልካም በሚባል ደረጃ ላይ ትገኛለች፡፡ እንደ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) መረጃ፤ በአውሮፓዊያኑ 2026 በአፍሪካ ትልቅ የኢኮኖሚ ዕድገት ካስመዘገቡ ሀገራት መካከል 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች፡፡

የጋና ምጣኔ ሃብት 46 በመቶ የሚሆነው እንደ ቴሌኮሙኒኬሽን፣ ዲጂታል ቴክኖሎጂ፣ ንግድ፣ ቱሪዝም እና ገንዘብ የመሳሰሉ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ላይ ጥገኛ የሆነ ነው፡፡ 31 በመቶ የሚሆነው ምጣኔ ሃብቷ ደግሞ ኢንደስትሪ ላይ የተመሰረተ ነው፡፡

ኢንደስትሪውም በብዛት ወርቅ፣ ነዳጅ እና ሌሎች ማዕድናትን በማምረት የውጭውን ገበያ መቆጣጠር ላይ ያማተረ ነው፡፡ ግብርናው በሌላ መልኩ 23 በመቶ ነው ለምጣኔ ሃብቷ አበርክቶ ያለው፡፡

ከሰሞኑ አዲስ ያለችውን ግኝት ለዓለም ማህበረሰብ ይፋ አድርጋለች፡፡ በሀገሪቱ ምዕራባዊ ክልል በነበራቸው ጉባኤ ወቅት ይህንኑ ያበሰሩት የሀገሪቱ ፕሬዝደንት ጆን ድራማኒ ማሃማ፤ ከጋና የባህር ዳርቻ 148 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ የሚገኝ ሃይድሮ ካርበን መገኘቱን ነው የገለጹት፡፡

ይህም ማለት ከርሰ ምድር ውስጥ ቁፋሮ ተደርጎ ከሃይድሮጅንና ካርበን የተዋቀረ ድፍድፍ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ክምችት ያለው አለት ነው የተገኘው፡፡ ፕሬዝደንት ድራማኒ ማሃማ ግኝቱ ጋና አዲስ የስነ-ምድር አቅም እንዳላት ማሳያ ነው ብለዋል፡፡

ተጨማሪ አዲስ ድፍድፍ ዘይት እና የተፈጥሮ ጋዝ ለማግኘት ተስፋ የሰነቁበት ስለመሆኑም ጠቆም አድርገዋል፡፡

ሃይድሮ ካርበኑ 2 ሺህ 289 ሜትር ጥልቀት ባለው ውሃ ውስጥ ተቆፍሮ እንደተገኘ ተገልጿል፡፡ ክምችት ያለበት ስፍራው 1 ሺህ 454 ስኩዌር ኪሎ ሜትር ሳይሸፍን እንዳልቀረ ተገምቷል፡፡

ሀይድሮ ካርበኑ በእርግጥም ነዳጅ ነው ወይስ የተፈጥሮ ጋዝ የሚለውን የመለየት ሥራ በቀጣይ እንደሚሰራ የዓለም መገናኛ ብዙሃን በመረጃቸው አስፍረዋል፡፡

ይህን ተከትሎ የጋና ማዕድን ሚኒስትሩ ጆን ጂናፖር በሰጡት መግለጫ ግኝቱ የማዕድንና አምራች ዘርፉን ለማነቃቃት እንዲሁም ኢንቨስትመንትን ለመሳብ አዲስ ምዕራፍ ከፍቷል ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

አፍሪካን ኒውስ እና ሮይተርስ በዘገባቸው እንዳሰፈሩት፤ ጋና እስካሁን ድረስ ለንግድ የሚሆኑ የነዳጅና የጋዝ ግኝቶችን በዋነኛነት ከአሸዋማ አለት ክምችቶች ውስጥ ነበር የምታገኘው፡፡

የጋና ታይምስ ጋዜጣ ደገግሞ የሀገሪቱን የኢነርጂ እና አረንጓዴ ሽግግር ሚኒስቴር መረጃን ጠቅሶ እንደዘገበው፤ ሀገሪቱ እስከ 126 ሺህ በርሜል ድፍድፍ ነዳጅ በቀን ታመርታለች፡፡

አዲሱ የሃይድሮ ካርበን ግኝቱ በቀጣይ ጋና በዘርፉ ትልቅ እመርታ እንደምታመጣ ታምኖበታል፡፡

ዘጋቢ፡- ኢያሱ ታዴዎስ