የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዜጎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ የሚጠብቅ አገልግሎት መሆኑ ተገለጸ
የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዜጎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ የሚጠብቅ ወሳኝ አገልግሎት መሆኑን የጎፋ ዞን አስተዳደር አስታውቋል፡፡
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ የ2019 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምና የቀጣይ 100 ቀናት ዕቅድ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዞናዊ የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ፣ የጤና መድህን ዜጎች በህመም ወቅት ሳይጨነቁ የህክምና አገልግሎት እንዲያገኙና ያልታሰበ ወጪን እንዲቋቋሙ የሚያግዝ መሆኑን ገልጸዋል።
የጤና አገልግሎት ተደራሽነትን ከማስፋት ባለፈ ዜጎችን ከድንገተኛ የህክምና ወጪ የሚጠብቅ ወሳኝ አገልግሎት መሆኑንም ተናግረዋል።
አዳዲስ አባላትን የመመዝገብና የነባር አባላትን እድሳት በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ስራ እንዲጠናከርም በአጽንኦት አንስተዋል።
የጎፋ ዞን ጤና መምሪያ ኃላፊ ዶክተር ንጉሴ መኮንን በበኩላቸው፤ በጤና ዘርፍ ተጨባጭ ውጤት ማስመዝገብና ለማህበረሰቡ ጥራት ያለው፣ ፍትሃዊና ተደራሽ አገልግሎት መስጠት እንዳለበት አሳስበዋል።
በዘንድሮው በጀት ዓመት የአባላትን ቁጥር ለማሳደግና የመድህኑን የፋይናንስ ዘላቂነት ለማጠናከር ትኩረት እንደሚሰጥ አመልክተዋል።
በመድረኩ የመምሪያው የ2019 የመጀመሪያ ሩብ ዓመት አፈጻጸምና የቀጣይ 100 ቀናት ዕቅድ እንዲሁም የማህበረሰብ አቀፍ ጤና መድህን ዞናዊ የንቅናቄ ሰነድ በመምሪያው ከፍተኛ ባለሙያዎች ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት፤ ጤናማና ምርታማ ማህበረሰብ ለመፍጠር በሁሉም ዘርፍ ውጤታማ ተግባራትን ለማከናወን ቁርጠኛ መሆናቸውን አንስተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ጤና ቢሮ ምክትል ኃላፊና የፕሮግራሞች ዘርፍ ኃላፊ አቶ ናፍቆት ብርሃኑ በበኩላቸው፤ የጤና መድህን ሽፋንን ለማስፋትና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት በማጎልበት የተቀመጠውን ዕቅድ ለማሳካት በሁሉም መዋቅሮች የተቀናጀ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል።
በቀጣይ የጤና አገልግሎትን ጥራትና ተደራሽነት ማሻሻል፣ የጤና ባለሙያዎችን ብቃትና ስነምግባር ማጠናከር፣ የጤና መረጃ አያያዝን ማዘመን፣ አንቡላንስ ለእናቶች አገልግሎት ብቻ ማዋል ዋና ዋና የትኩረት መስኮች መሆናቸውን ገልጸዋል።
በመድረኩ በ2018 በጤና መድህን አፈጻጸም የተሻለ ውጤት ያስመዘገቡ ግለሰቦች፣ ድርጅቶችና መዋቅሮች ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።
በመድረኩ የዞን፣ የወረዳና የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን

More Stories
በሆስፒታሉ የተሻለ አገልግሎት መሰጠት በመጀመሩ ከአላስፈላጊ ወጪና እንግልት መዳናቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ ሙዱላ መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል አገልግሎት ለማግኘት በመጡበት ያነጋገርናቸው ተገልጋዮች ተናገሩ
በኮሬ ዞን የእንስሳት በሽታዎችን ለመከላከል የተጀመረው የክትባት ዘመቻ ተጠናክሮ ቀጥሏል
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በጤናው ዘርፍ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የወላይታ ዞን አስተዳደር ገለጸ