የዝውውር ጭምጭምታዎች አቋሜ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል – ቪኒሺየስ ጁኒየር

የዝውውር ጭምጭምታዎች አቋሜ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል – ቪኒሺየስ ጁኒየር

የሪያል ማድሪዱ የፊት መስመር ተጫዋች ቪኒሺየስ ጁኒየር፣ በክረምቱ የዝውውር መስኮት ወቅት የነበሩ የዝውውር ጭምጭምታዎች ከፍተኛ ጫና ውስጥ ከተውት እንደነበርና ይህም በውድድር ዓመቱ መጀመሪያ ላይ ላሳየው ደካማ አቋም ምክንያት መሆኑን ገልጿል።

በአሰልጣኝ ሆዜ ሞሪንሆ በሚመራው ሪያል ማድሪድ በዘንድሮው የውድድር ዘመን 12 ጨዋታዎችን ያደረገው የ26 ዓመቱ ኮከብ፣ ማስቆጠር የቻለው አንድ ግብ ብቻ ሲሆን ሦስት ግብ የሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

ተጫዋቹ በሪያል ማድሪድ የነበረው ኮንትራት የመጨረሻ ዓመት ላይ በመድረሱ ምክንያት፣ አዲስ ውል ከመፈረሙ በፊት ወደ እንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ ሻምፒዮኑ አርሰናል ሊዘዋወር ይችላል የሚሉ ሰፊ ዘገባዎች ሲወጡ ነበር።

ቪኒሺየስ ከዝውውሩ ጫና በተጨማሪ ብራዚል በዓለም ዋንጫው በጥሎ ማለፍ (16 ውስጥ) መሰናበቷን ተከትሎ በቂ ልምምድ አለመስራቱንም ተናግሯል።

ተጫዋቹ ስለ ሁኔታው ሲያብራራ«ከዓለም ዋንጫው በኋላ የሚገባኝን ያህል በሚገባ አልተዘጋጀሁም፤ ምክንያቱም የዚያ ውድድር ተጽዕኖ ለሁሉም ብራዚላውያን እጅግ ከባድ ነው። በውድድሩ በጊዜ መሰናበታችን ያልጠበቅነው ነገር ነበር። በዚህም ምክንያት የእረፍት ጊዜዬን ለመዝናናት እና ከቤተሰቦቼ ጋር ብዙ ጊዜ ለማሳለፍ ተጠቀምኩበት፤ ከቀደሙት ዓመታት ባነሰ ሁኔታም ልምምድ ሰራሁ። ይህ ደግሞ በውድድር ዓመቱ አጀማመሬ ላይ ተጽዕኖ ሳያሳድር አልቀረም» ብሏል።

ተጫዋቹ አክሎም «ከዚህ በተጨማሪ ከኮንትራት እድሳቴ ጋር በተያያዘ ባለፈው ክረምት በርካታ ክለቦች ፍላጎት በማሳየታቸውና በሪያል ማድሪድ በነበረው ሁኔታ በጣም ተጨናንቄ ነበር። ሆኖም የውድድር ዓመቱ ገና በጣም ረጅም ነው በቅርቡ ወደ ጥሩ አቋሚ እመለሳለሁ» ሲል ተስፋውን ገልጿል።

ባለፉት አምስት ተከታታይ የውድድር ዘመናት በእያንዳንዳቸው ከ20 በላይ ግቦችን በማስቆጠር የማድሪድ የፊት መስመር ወሳኝ ኃይል የነበረው ቪኒሺየስ፣ ባለፈው ጥቅምት ወር የቪያሪያሉን አማካይ ናታን ሳሊባን ፀጉር በመጎተት በፈጸመው ጥፋት በቀጥታ ቀይ ካርድ ከሜዳ ተወግዶ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ተላልፎበት ነበር።

የእርሱን መታገድ ተከትሎ የክለቡ ሪከርድ ፈራሚ የሆነው ያን ዲዮማንዴ በግራ መስመር አጥቂነት ቦታ ያገኘውን ዕድል በሚገባ በመጠቀም አራት ግቦችን አስቆጥሮ ጥሩ ብቃቱን አስመስክሯል።

ይህም ቪኒሺየስ ቋሚ ቦታውን ለማስመለስ ጠንካራ ፉክክር እንደሚጠብቀው አመላካች ሆኗል።

እ.ኤ.አ. በ2018 ከብራዚሉ ፍላሜንጎ ሪያል ማድሪድን የተቀላቀለው ቪኒሺየስ፣ ቡድኑን ወደ ቀድሞ አስፈሪነቱ ለመመለስ በሚደረገው ጥረት ላይ ትኩረቱን አድርጓል።

በሆዜ ሞሪንሆ የሚመራው ሪያል ማድሪድ በአሁኑ ወቅት በላሊጋው መሪ ከሆነው ተቀናቃኙ ባርሴሎና በሦስት ነጥቦች አንሶ ሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ ሲሆን፣ በመጪው ቅዳሜ በሜዳው ሴልታ ቪጎን ያስተናግዳል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ