ዴክላን ራይስ በአርሰናል ቤት ለተጨማሪ ዓመታት የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ለመፈረም ተስማማ

ዴክላን ራይስ በአርሰናል ቤት ለተጨማሪ ዓመታት የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ለመፈረም ተስማማ

እንግሊዛዊው የመሃል ሜዳ ተጫዋች ዴክላን ራይስ በአርሰናል ቤት እ.ኤ.አ እስከ 2031 ድረስ የሚያቆየውን አዲስ የአምስት ዓመት ውል ለመፈረም ከስምምነት ላይ ደርሷል።

ለድርድሩ ቅርብ የሆኑ ምንጮች እንደገለጹት ከሆነ፣ የ27 ዓመቱ አማካይ ለክለቡም ሆነ ለብሔራዊ ቡድኑ እያበረከተ ላለው የላቀ አስተዋጽኦ እውቅና የሚሰጠውን ይህንን አዲስ ኮንትራት በቅርቡ በይፋ ይፈርማል ተብሎ ይጠበቃል።

ራይስ በ2023 ከዌስትሃም ዩናይትድ በ100 ሚሊዮን ፓውንድ (ተጨማሪ 5 ሚሊዮን ፓውንድ ጉርሻን ጨምሮ) ክለቡን ሲቀላቀል የፈረመው ነባር ውል እስከ 2028 የሚቆይ ሲሆን፣ ተጨማሪ የ12 ወራት ማራዘሚያ አማራጭም ነበረው።

ዴክላን ራይስ አርሰናል ባለፈው የውድድር ዘመን ከ22 ዓመታት በኋላ የፕሪሚየር ሊጉን ዋንጫ ዳግም እንዲያነሳ ቁልፍ ሚና ተጫውቷል።

በሊጉ 36 ጨዋታዎችን አድርጎ 4 ግቦችን ሲያስቆጥር 7 ለግብ የሚሆኑ ኳሶችን አመቻችቶ አቀብሏል።

በተጨማሪም መድፈኞቹ ከ20 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ለአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍጻሜ ደርሰው በፓሪስ ሴንት ዠርሜን በመለያ ምት እስከተሸነፉበት ጨዋታ ድረስ፣ ራይስ በሁሉም ውድድሮች 55 ጊዜ ተሰልፎ ተጫውቷል።

እስካሁን ለአርሰናል በአጠቃላይ 173 ጨዋታዎችን ያደረገ ሲሆን፣ 22 ግቦችን በማስቆጠርና 36 አሲስቶችን በማድረግ ድንቅ ብቃቱን አሳይቷል።

የራይስ ስምምነት አርሰናል ዋና ዋና ኮከቦቹንና አሰልጣኙን በክለቡ የማቆየት ስትራቴጂ አካል ነው።

አሰልጣኝ ሚኬል አርቴታ ባለፈው ጥቅምት ወር የአራት ዓመት አዲስ ኮንትራት መፈረማቸው የሚታወስ ሲሆን፣ ሆላንዳዊው ተከላካይ ጁሪየን ቲምበርም ውሉን ለማራዘም ከክለቡ ጋር መስማማቱን ዘ አትሌቲክ ዘግቧል።

ይህ ተከታታይ የውል ማደስ ዕርምጃ አርሰናል ያገኘውን ድል ለማስቀጠልና በአውሮፓ መድረክ ይበልጥ ተፎካካሪ ሆኖ ለመዝለቅ ያለውን ጠንካራ ፍላጎት የሚያሳይ ነው።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ