ከባሎን ዶር እስከ ሴሪ ሲ
የብራዚል እና የዓለም እግር ኳስ ፈርጥ የነበረው ሮናልዲኒሆ፤ ከፕሮፌሽናል እግር ኳስ ህይወት ራሱን ካገለለ ከ11 ዓመታት በኋላ በ46 ዓመቱ በጣሊያን ሶስተኛ ዲቪዚዮን (ሴሪ ሲ) የሚሳተፈው የራቬናን ማልያ ለብሶ ወደ ሜዳ በመመለስ የስፖርቱን ዓለም አስገርሟል።
ትናንት እሁድ ራቬና ከፎርሊ ጋር ባደረገው የደርቢ ጨዋታ ላይ በቋሚ ተሰላፊነት ጨዋታውን የጀመረው ሮናልዲኒሆ፤ ወደ ሜዳ የተመለሰበት ዋነኛ ምክንያት ከክለቡ ፕሬዝዳንት ኢግናዚዮ ቺፕሪያኒ ጋር ባለው የቅርብ ወዳጅነት መሆኑ ተገልጿል።
ፕሬዝዳንቱ ሃሳቡን ሲያቀርብለት ሮናልዲኒሆ ደስታን እና መነቃቃትን ለመፍጠር ሲል ወዲያውኑ መስማማቱ ተነግሯል።
ከዚህ በተጨማሪም ሮናልዲኒሆ እንደ ማይክል ጆርዳን ሁሉ የራሱን የስፖርት አልባሳት እና ቁሳቁሶች ብራንድ “R10″ን ለማስተዋወቅ እንደ ትልቅ የማስታወቂያ መድረክ ለመጠቀም ማሰቡ እንዲሁም በእግር ኳስ ህይወቱ 299 ጎሎችን አስቆጥሮ ጫማውን የሰቀለው ጥበበኛው ተጫዋች፣ የመጨረሻውን 300ኛ ጎል በማስቆጠር ታሪኩን ለማጠናቀቅ ያለመ ጉዞ ለዝውውሩ ሌሎች ሁለት ዋና ዋና ዓላማዎች ናቸው።
በስታዲዮ ብሩኖ ቤኔሊ የተደረገውን ይህንን ያልተለመደ ክስተት ለመታደም ተጨማሪ 1,800 ጊዜያዊ መቀመጫዎች ተዘጋጅተው ስታዲየሙ በደጋፊዎች ተሞልቷል።
በስፍራውም የሮናልዲኒሆ የቀድሞ የቡድን አጋር ብራዚላዊው ግብ ጠባቂ ዲዳ፣ ታዋቂው የጣሊያን የቴኒስ ተጫዋች ፋቢዮ ፎግኒኒ እና የቀድሞው የፎርሙላ ዋን አመራር ፍላቪዮ ብሪያቶሬ ተገኝተው ጨዋታውን ተከታትለዋል። ጨዋታውም በስካይ ስፖርት የዩቲዩብ ቻናል በቀጥታ ተላልፏል።
በመጀመሪያው አጋማሽ በታዋቂው የፀጉር ማሰሪያው እና በሽበት በተወረረው ረጅም ፀጉሩ ወደ ሜዳ የገባው ሮናልዲኒሆ፣ የቀድሞ ፍጥነቱ ቢቀንስም አንዳንድ ማራኪ ቅብብሎችን ሲያደርግ እና የማዕዘን ምቶችን ሲመታ ታይቷል።
በ35ኛው ደቂቃ ላይ ጁሊዮ ዶናቲ ከርቀት ያስቆጠረው ድንቅ ጎል ከመገኘቱ በፊት፣ ሮናልዲኒሆ ለጎሉ መገኘት መነሻ የሆነውን ቀላል ቅብብል በማድረግ ቡድኑን ቀዳሚ እንዲሆን አግዟል።
ይሁን እንጂ 300ኛ ጎሉን ለማስቆጠር ያደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቶ በእረፍት ሰዓት ተቀይሮ ወጥቷል።
ከእሱ መውጣት በኋላ ራቬና ተጨማሪ ጎል አስቆጥሮ ጨዋታውን 2-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።
ሮናልዲኒሆ በእረፍት ሰዓት ለስካይ ኢታሊያ በሰጠው አስተያየት “እግር ኳስ ለእኔ ሁልጊዜም እንዲህ ነው። ይህ የመጨረሻ ጨዋታዬ ይሆን? አላውቅም፤ ፕሬዝዳንቱ መጥራቱን ከቀጠለ ተመልሼ እመጣለሁ!” ሲል ተናግሯል።
ምንም እንኳን ክስተቱ በፕሮፌሽናል ውድድር ላይ የተደረገ የማስታወቂያ ስልት ተደርጎ ቢተችም፣ በርካታ የእግር ኳስ አፍቃሪያን ግን የዘመኑን ታላቅ ጥበበኛ ዳግም በሜዳ ላይ በማየታቸው ልዩ ደስታን አግኝተዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ከባሎን ዶር እስከ ሴሪ ሲ

More Stories
ዴክላን ራይስ በአርሰናል ቤት ለተጨማሪ ዓመታት የሚያቆየውን አዲስ ኮንትራት ለመፈረም ተስማማ
የዝውውር ጭምጭምታዎች አቋሜ ላይ ተጽዕኖ አሳድረዋል – ቪኒሺየስ ጁኒየር
ሮሜሉ ሉካኩ ከቤልጂየም ብሔራዊ ቡድን ራሱን ማግለሉን አስታወቀ