“ጅምር የግብርና ምርምር ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ተመራማሪዎች በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው” – ዶክተር ዮሐንስ ሆራሞ

“ጅምር የግብርና ምርምር ሥራዎችን ውጤታማ ለማድረግ ተመራማሪዎች በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው” – ዶክተር ዮሐንስ ሆራሞ

የዛሬ የንጋት እንግዳችን ዶክተር ዮሐንስ ሆራሞ ይባላሉ፡፡ በዋቸሞ ዩንቨርሲቲ ምርምርና ተቋማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተርና መምህር ናቸው፡፡ በዩኒቨርሲቲው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የሚያግዙ የምርምር ውጤቶችን ከማፍለቅና ከማስተዋወቅ ረገድ የተሰሩ ስራዎች ምን ይመስላሉ በሚለው ዙሪያ ማብራሪያ እንዲሰጡን ቆይታ አድርገናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡

በመለሰች ዘለቀ

ንጋት፡- ስለፈቃደኛነትዎ በዝግጅት ክፍሉ ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡

ዶክተር ዮሐንስ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡

ንጋት፡- ራስዎን ቢያስተዋውቁ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- ተወልጄ ያደኩት በሀዲያ ዞን ሶሮ ወረዳ ነው፡፡ በግብርና የሚተዳደር ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደኩት፡፡ ከግብርና ስራ ጋር ጥብቅ ቁርኝትና ትስስር አለኝ፡፡ የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ግንብቹ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው የተከታተልኩት። የሁለተኛና ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ በየካቲት ትምህርት ቤት ተከታትያለሁ፡፡

ከ1977ዓ.ም እስከ 1978ዓ.ም በወንዶ ገነት ደን ኮሌጅ በደን ልማት የዲፕሎማ መርሃ ግብር ተከታትያለሁ። በሙያዬ በሀዋሳ ደን እፅዋት ምርምር ማእከል የፌዴራል ተጠሪ/ተወካይ ሆኜ ለ7 አመታት አገልግያለሁ፡፡

ከዚያም ወደ ሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ተዛወርኩ፡፡ በስራ ላይ ሆኜ በመንግስት በተመቻቸልኝ ዕድል በወንዶ ገነት ደን ኮሌጅ በደን ልማት የመጀመሪያ ድግሪዬን እንዲሁም በዚያው ኮሌጅ በጥምር ግብርና ሁለተኛ ድግሪዬን ከያዝኩ በኋላ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲን ተቀላቀልኩ፡፡ በ2005ዓ.ም በዩንቨርሲቲው የግብርና ኮሌጅ ሲመሰረት መስራች ሆኜ ስራ ጀመርኩ፡፡

ዩኒቨርሲቲው ባመቻቸልኝ የትምህርት እድል የሶስተኛና የዶክትሬት ድግሪዬን በኢንቫይሮሜንታል ማኔጅመንት /በአካባቢ አያያዝ/ ተከታትያለሁ፡፡ በአሁኑ ጊዜ በዩኒቨርሲቲው በግብርና ኮሌጅ መምህር እና የምርምር ተቋማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ሆኜ እያገለገልኩ እገኛለሁ። በመንግስት መስሪያ ቤት በሙያዬ 36 አመታት አገልግያለሁ፡፡

ንጋት፡- በዩኒቨርሲቲው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሰሩ ስራዎች እንዴት ይገለጻሉ ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- እንደ ዋቸሞ ዩኒቨርሲቲ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያስችላል ብለን እምነት የጣልንባቸውን ቴክኖሎጂዎችን የማመንጨት ስራ እየተሰራ ነው፡፡ ግብርና መሰረት ያደረገው በ3 መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ነው፡፡

እነዚህም በሰብል፣ በእንስሳት ሀብትና በተፈጥሮ ሀብት ላይ ነው። እንደ ዩኒቨርሲቲው 7 የግብርና ምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት አሉ፡፡ እነሱም ዋናው ግቢ፣ ለምቡዳ፣ ቡኡማ፣ ሾንቆላ፣ ሾኔ፣ ኦርጫ፣ ዱራሜ ካምፓስ ናቸው፡፡ በእነዚህ ማእከላት ለአርሶ አደሩ ይጠቅማል፣ ምርታማነትን ያሳድጋል፣ የምንላቸውን ቴክኖሎጂዎችን የማላመድና የማሰራጨት ስራ ይሰራል፡፡

ለምሳሌ ቡና ለአካባቢው ማህበረሰብ ትልቅ የገቢ ምንጭ በመሆኑ ምርታማነቱን የሚያሳድጉ ቴክኖሎጂዎችን የማሰራጨት ተግባር እየተከናወነ ይገኛል፡፡ የቡና ችግኝን ከምርምር ተቋማት በማምጣት በሾንቆላ፣ በለምቡዳ፣ በሾኔ፣ በዱራሜ፣ በማባዛት ለአርሶ አደሩ እናሰራጨለን። ይህ በምርምር የተገኘው ቡና በአንድ አመት ውስጥ ችግኝ ተፈልቶ ይደርሳል። ችግኙ ከተተከለ በሶስተኛ አመት ላይ ማፍራት ይጀምራል፡፡ ምርትም ይሰጣል፡፡

ንጋት፡- በግቢው ውስጥ የሚሰሩ  የምርምር ስራዎች ተግባር ምን ይመስላል?

ዶክተር ዮሐንስ፡- ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ስራዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡

በዩኒቨርሲቲው ዋና ግቢ ውስጥ ብቻ በ95 ሄክታር መሬት ላይ የግብርና ምርምር ስራዎች ይከናወናሉ። የእንስሳት መኖ በ4.5፣ የሰብል ልማት በ13፣ እንሰት በ3.5፣ አቮካዶ በ3.5፣ አፕል በ1፣ እንዲሁም ቡና በ1 ነጥብ 5 ሄክታር መሬት ላይ እየተባዛ ይገኛል፡፡

በምርታማነታቸውና በሽታን በመቋቋም የተረጋገጡ ማህበረሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ የግብርና ምርምር ስራዎች ላይ ትኩረት አድርገን እየሰራን እንገኛለን፡፡

ዩኒቨርሲቲው በተለይም በእንሰት ምርት ላይ በትኩረት እየሰራ ይገኛል። በምርታማነታቸው የተረጋገጡ፣ በአጭር ጊዜ የሚደርሱና በሽታን መቋቋም የሚችሉ የእንሰት ዝርያዎችን አባዝቶ ለማህበረሰቡ ለማድረስ እየሰራ ነው፡፡

የአፕል ምርታማነትን ለማሳደግ በለምቡዳ ማዕከል ላይ የማዳቀል፣ የማለማመድና ለአርሶ አደሮች የማዳረስ ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ዩኒቨርሲቲው ምርታማነቱ የተረጋገጠ የስንዴ ዝርያን በምርምር ያረጋገጠ ሲሆን ለግብርና ሚኒስቴር ቀርቦ ውጤቱ እየተጠበቀ ይገኛል። በዘንድሮ ክረምት አንድ ዙር ተዘርቶ ውጤታማነቱ ከተረጋገጠ በኋላ ለማህበረሰቡ እንዲደርስ የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡

ንጋት፡- የእንስሳት ምርትና ምርታማነትን ከማሳደግ አኳያ የተሰሩ ስራዎችስ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- የእንስሳት ምርታማነትን ከማሳደግ ረገድ በዩኒቨርሲቲው ስር ባሉ ስምንት ማእከላት ላይ የተሻሻለ ዝርያ ያላቸው ኮርማዎችን ለአርሶ አደሮች ለማድረስ እየተሰራ ነው፡፡ ዝርያዎቹ ከአካባቢው አየር ጸባይ ጋር የሚስማሙና የወተት ምርታማነታቸውም የተረጋገጠ ነው፡፡ በዩንቨርሲቲው ሶስት አይነት የእንስሳት ዝሪያዎች አሉ፡፡ ቦረና፣ ሆልስቴን እና ጄርሲ የሚባሉ ናቸው፡፡ እነዚህን ዝርያዎች ከኮርማዎቹ ጋር እናዳቅላለን። አርሶ አደሮቹ ከማዕከላቱ የኮርማ አገልግሎት እንዲያገኙና ዝርያዎችን እንዲያሻሽሉ የማድረግ ስራ ይሰራል፡፡ ከዚያም ባሻገር የወተት ምርትን ለግቢው ማህበረሰብ በቅናሽ ዋጋ እናቀርባለን፡፡

በግቢው በምርምር የተረጋገጡ በቀን ከ5 እስከ 6 ሺህ እንቁላል ምርት የሚሰጡ ከ150 ሺህ በላይ ዶሮዎች አሉ። ይህም ከግቢው ማህበረሰብ ፍጆታ አልፎ በከተማ ባሉ ማዕከላት ይሸጣል። የደቡብ አፍሪካ ፍየልና የቦንጋ የበግ ኮርማዎችን የማባዛትና የማሰራጨት ስራም ይሰራል፡፡

እነዚህ እንስሳትን መመገብ የምንችልበት በዋናው ግቢ ከ4 ሄክታር መሬት ላይ የመኖ ልማት ስራ ይሰራል፡ ፡ አራት አይነት የመኖ ዝርያዎች አሉ፡፡ እነዚህ ዝርያዎች የምርምር ደረጃዎችን  ጨርሰው ስለወጡ የማባዛትና ለአርሶ አደሩ የማድረስ ስራ እየተሰራ ይገኛል። ከዚህም ባሻገር 20 የሚሆኑ የእንስሳት መኖ ዝርያዎችን ከአለም አቀፍ የእንስሳት ምርምር ማእከል ጋር በመተባበር ምርምር እያካሄድንበት እንገኛለን፡፡

በአሁኑ ጊዜ የመሬት ጥበት ችግር እየተስተዋለ በመምጣቱ ጥምር ግብርና ላይ ትኩረት አድርገን እንሰራለን። ይህም በትንሽ ቦታ ላይ ብዙ ምርት ለማምረት ያስችላል፡፡ ከዚህም ባሻገር የመሬት ለምነትንም ያስጠብቃል። ሙያዬም ጥምር ግብርና ስለሆነ ዘርፉ የሚያስገኘውን ጠቀሜታ ከግንዛቤ በማስገባት በልዩ ትኩረት እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፡- እንደ ሀገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ ስራን በምርምር የመደገፍ ስራ ምን ይመስላል?

ዶክተር ዮሐንስ፡- እንደ ሀገር የተጀመረውን የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብርን ከመተግበር አንጻር ዩንቨርሲቲው ትኩረት አድርጐ እየሰራ ነው፡፡ በምርምር የተገኙና ሀገር በቀል ችግኞችን በማባዛት የማሰራጨት ስራ ይሰራል፡፡ የሾንቆላ ተራራ አናትን ለማልማት የተፋሰስ ስራዎች ተሰርተዋል፡፡

በተራራው ላይ 300ሄክታር መሬት ተከልሎ የደን ልማት ስራ እየተሰራ ይገኛል፡፡ ዘርፈ ብዙ  ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞችም እዚያው እየፈሉ ይተከላሉ። በዚህ ለ27 ሰዎች የስራ እድል ተፈጥሮላቸዋል፡፡

አምና በዋና ግቢ ብቻ 5 ሺህ የአቮካዶ፣ 3 ሺህ የአፕል እና 10 ሺህ የቡና ችግኞች በታቀደው መሠረት ተተክለዋል። ዩኒቨርሲቲው የመማር ማስተማር፣ የማህበረሰብ አገልግሎትና የምርምር ስራዎች አገልግሎት ይሰጣል፡፡ የኛ ዘርፍ ደግሞ በምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ላይ ነው ትኩረት አድርጎ የሚሰራው፡፡ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን የማመንጨትና የማላማድ ስራ እንሰራለን፡፡

ውብና ማራኪ አካባቢ ከመፍጠር ባለፈ ለአፈር ለምነትና ለምግብ ዋስትና የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ በመሆኑ ለዘርፉ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ይገኛል፡፡

ንጋት፡- የግብርና ስራን ውጤታማ ለማድረግ ከማን ምን ይጠበቃል ይላሉ?

ዶክተር ዮሐንስ፡- እኔ የአርሶ አደር ልጅ ነኝ፤ ማሳ ላይ ነው ያደኩት። ኢትዮጵያ ዕምቅ የተፈጥሮ ሀብት እና ሰፊ የሰው ኃይል ያላት ሀገር ናት። ከዚህ አንጻር ጅምር የግብርና የምርምር ሥራዎች ከዳር እንዲደርሱ ተመራማሪዎችና ባለድርሻ አካላት መስራት አለባቸው፡፡

የተጀመሩ ሁለንተናዊ የምርምር ሥራዎች ከግብ እንዲደርሱ የግለሰቦች ጥረት እንዳለ ሆኖ መንግሥት ለዘርፉ የሚሰጠው ትኩረት ግን ወሳኝነት አለው፡፡ በሀገራችን 80 ከመቶ በላይ የሆነው የማኅበረሰብ ክፍል የሚተዳደረው በግብርና ስራ በመሆኑ ዘርፉን ለማዘመንና ምርታማነትን ለማሳደግ ተመራማሪዎች የበኩላቸውን ኃላፊነት መወጣት አለባቸው፡፡

መንግሥት የሀገሪቱ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነውን ግብርና ውጤታማ እንዲሆን የበለጠ ትኩረት መስጠት ይኖርበታል።

ተመራማሪዎች ምርትና ምርታማነትን የሚያሳድጉ የምርምር ስራዎችን በመስራትና በማስፋት በቁርጠኝነት መስራት አለባቸው፡፡ የአካባቢው ማህበረሰብም ዩኒቨርሲቲውን እንደ እርዳታ ድርጅት መጠበቅ ሳይሆን በምርምር የተገኙ ውጤቶችን በመጠቀም ምርታማነታቸውን ለማሳደግ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ንጋት፡- ስለነበረን ቆይታ እናመሰግናለን፡፡

ዶ/ር ዮሐንስ፡- እኔም አመሠግናለሁ።