በአንዱዓለም ሰለሞን
“ምርቃት” መልካም ነገር ነው፡፡ መመረቅ መባረክ ነው፡፡ “ወልደህ ሳም” ያለን ወላጅ “ወልደህ እየው” ብሎ ካለን ግን ነገሩ ምርቃት ብቻም አይደለም ማለት ነው፡፡ እርግማን ባንለውም እንድናስተውለው የሚገባ አንዳች ነገር አለ፡፡ … የምንመረቀው አንድም በዕውቀት፣ አንድም ደግሞ በጥበብ ነው፡፡ በጥበብ ሲሆን ደግሞ የበለጠ ጥሩ ይሆናል፡፡ ያወቅነውን ለመተግበር ጥበብ ያስፈልጋልና፡፡ የራስን ህይወት በአግባቡ ለመምራት፣ ለችግሮች መፍትሄ ለማበጀት፣ ከዚያም ከፍ ሲል ከራስ አልፎ ሌሎችን ለመርዳት፣ ለሀገር አንዳች ለማበርከት ያልጠቀመ እውቀት ምን ዋጋ አለው?… እናም ዕውቀትን ከመፈለግ ባሻገር ጥበብን መሻት ለአንድ ሰው በእጅጉ አስፈላጊ ነው፡፡
ነገሬን ባስቀድምም ሠላምታዬን አልዘነጋሁትምና እነሆ እንደምን ከርማችኋል ብዬ ብል፤ ምነው “ከፈረሱ ጋሪው” ቀደመ ትሉኝ ይሆን? እርግጥ ነው፤ ሁሉን እንደቅደም ተከተሉ፣ እንደ ጊዜውና ሁኔታው፣ እንደ ወግና ባህሉ አይተንና መዝነን በማስተዋል እናደርግ ዘንድ ጥበብን ያድለን እያልኩ ልቀጥል፡፡ የዛሬው ወጌ መነሻ የሰሞኑ ትዝብቴ ነው። የታዘብኩት ደግሞ ራሴን ነው፡፡ ሰሞኑን የነርሰሪ ተማሪ ልጄን ለማስመረቅ ከእሱ ጋር ከቦታው ተገኝቼ ነበር፡፡ አዳራሹ ውስጥ ከአንድ የልጄ ጓደኛ አባት ጋር ተቀምጠን የምረቃ ስነ ስርዓቱን እየተከታተልን ቆየን፡፡ ዝግጅቱ ደስ የሚል ነበር፡፡
በደስታ የሚፈነድቁ ህጻናትን ማየትና በሀሴት የሚፍነከነኩ ወላጆችን መመልከት በራሱ ጥሩ ስሜትን የሚፈጥር ነገር ነው፡፡ እኔም ታዲያ በዚህ የደስታ ስሜት ውስጥ ሆኜ አንድ ትዝታ በሀሳብ ወደ ኋላ መለሰኝ። ከዓመታት በፊት ከዩኒቨርሲቲ ስመረቅ የሆነውን አስታወስኩና ለአፍታ በሀሳብ ነጎድኩ፡፡ የተማርኩበት ዩኒቨርሲቲ ተወልጄ ካደኩበትና ከምኖርበት ከተማ በብዙ ኪሎ ሜትሮች ይርቃል፡፡ በዚህ የተነሳ አባቴ ለምርቃቴ እንዳይመጣ፣ እሱን ለማሳመን ብዙ ጥረት አድርጌ ነበር፡፡ (ምንም እንኳ ባይሳካልኝም) በወቅቱ እኔ አስብ የነበረው የእሱን ልፋትና የሚያወጣውን “አላስፈላጊ ወጪ” ነበር፡፡ የዛኔ በምንም መልኩ ሊከሰትልኝ ያልቻለውና ያላስተዋልኩት ነገር ግን፤ እሱ ይህቺን ቀን ምን ያህል ይናፍቃት እንደነበር ነው፡፡
ያቺ ዕለት ለእሱ የብዙ ዓመታት ድካሙን የሚያይባት መሆኗን አልተገነዘብኩም ነበር፡፡ ነገሩን ከዚህ አንጻር ባለማየቴም በወቅቱ ይህን የአባቴን ስሜትና እውነት ሳልረዳለት ቀረሁ፡፡ ብስለት ማለት ባለን እውቀት ነገሮችን በተለያየ መልኩ ማየት ነው፡፡ በወቅቱ እኔ የጎደለኝም ይህ ነበር፤ ይህን ለማስተዋል የሚያስችል ጥበብ፡፡ እናም ታዲያ ዛሬ፣ አባቴ ያኔ “ስሜቴ የሚገባህ ስትወልድ ነው” ብሎኝ የነበረው፣ ልጄ ገና ከነርሰሪ ሲመረቅ ገባኝ እላችኋለሁ። “ወልደህ እየው” የሚሉት ለካ ይህንን ነው! … እውቀት የሌሎችን ስሜትና ችግር በእነርሱ ጫማ ውስጥ ሆነን እንድናይ ካላደረገን፣ ሰዎችን እንድንረዳ ካላበቃን እውቀትነቱ ምኑ ላይ ነው? ይህ እስካልሆነ ድረስ የያዝነው ዲግሪ ወይንም አውቀናል ያልነው ዕውቀት የመረጃ ቋት እንጂ አዋቂ አያሰኘንም፡፡
ይህን ሳስብ በአንድ ወቅት ከአንድ መጽሀፍ ላይ ያነበብኳቸው እውነታዎች ታወሱኝ፡- እውነተኛ ትምህርት አዕምሮንና ልብን ማሰልጠን ነው፡፡ አንድ ሰው ጥሩ ውጤትና ዲግሪ ኖሮት፤ ነገር ግን ብዙ ያልተማረ ሊሆን ይችላል፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን እንዳለው ማንበብ በማይችል ሰውና ማንበብ እየቻለ ግን ደግሞ በማያነብ ሰው መካከል ያለው ልዩነት ተመሳሳይ ነው። … አንድ ሰው ሊማረው የሚገባ ነገር “ለመማር መማር” ነው፡፡ አንዳንድ ሰዎች ግን ትምህርት እውነታን ከማስታወስ ችሎታ ጋር ይምታታባቸዋል፡፡ … ፕሮግራሙ አብቅቶ ወደ ቤት ተመለስን። እቤት ስንደርስ ልጄ አንድ ጥያቄ ጠየቀኝ፡- “ባቢ” “አቤት” “አንተና ማሚ አልተመረቃችሁም እንዴ?” “ተመርቀናል” አልኩት ቀጥሎ ሊያስከትል የሚችለውን ጥያቄ ለመገመት እየሞከርኩ፡፡
“የምርቃታችሁ ፎቶ የታለ ታዲያ?” ሁለታችንም በፎቶ ፍሬም ውስጥ አድርገን ያኖርነው የምርቃት ፎቶ እቤታችን ውስጥ የለም፡፡ ይህ ቢሆን ኖሮ ምላሹን ያቀልልኝ ነበር፡፡ ከኮመዲኖ ውስጥ፣ ካየሁት ዓመታት ያስቆጠርኩትን የፎቶ አልበም አወጣሁና ገጾቹን ገለጥ ገለጥ አድርጌ ብቸኛውን የምርቃት ፎቶዬን እያሳየሁት ፡- “ይኸው የእኔ ፎቶ፤ የእናትህን ደግሞ ራሷን ጠይቃት ” አልኩት፡፡ ፎቶውን ለአፍታ ትኩር ብሎ ሲያይ ቆየና፡- “ይሄ እኮ ከአደክ በኋላ ነው!?” አላለኝም። ለዚህ ጥያቄ ትክክለኛውን ምላሽ የሚሰጠው ጊዜ ነው፡፡ በእኛ ጊዜ እንዲህ እንደዛሬው የነርሰሪ ምርቃት አልነበረም፡፡
የምን የመመረቂያ ገዋን፣ የምን የመመረቂያ መጽሔት፡፡ … “ነገርን ነገር ያነሳዋል”፤ እንዲሉ፣ ስለመጽሔታቸው ሳነሳ ምን ትዝ አለኝ መሰላችሁ፤ መጽሄታቸው ላይ ካለው የየራሳቸው ፎቶ ስር፣ ነገ (ሲያድጉ) ምን ለመሆን እንደሚፈልጉ ለመምህራኖቻቸው በነገሯቸው መሠረት ይህን ፍላጎታቸውን የሚገልጽ የሙያ መስክ ነው የተጻፈው፡፡ የመጽሄቱን ገጾች እየገለጥኩ ስመለከት አንድ ያልጠበኩትን ነገር አየሁ፡፡ ወደ ፊት መሆን የሚፈልገውን ስጠይቀው አውሮፕላን አብራሪ ወይም መሀንዲስ ( በእሱ አገላለጽ ፎቅ ቤት መስራት ) ይለኝ የነበረው ልጅ ሀሳቡን በምን ምክንያት ቀይሮ “ፓሊስ” እንዳለ አልገባኝም፡፡ ይህ ነገር የከነከናት እናቱ ታዲያ፡- “ወደ ፊት የምሆነው ፓይለት ነው ስትል አልነበር፤ እንዴት ፖሊስ አልክ ? ” በማለት ስትጠይቀው ምን ቢላት ጥሩ ነው፡- “እና ታዲያ ሌባ ልበል! ” ብሏት እርፍ፡፡ ወደው አይስቁ አሉ፡፡
ነገሩ አንድ ቀልደኛ ጓደኛዬ እንዳለው ከሆነ ግን ጉዳዩ በሳቅ ብቻ የሚታለፍ አይደለም፡፡ የእኔን ልጅ ጨምሮ ከፎቷቸው ስር “ፖሊስ” በሚል የተጻፈላቸው ልጆች ቁጥር ብዙ መሆኑን ለመታዘብ ችያለሁ፡፡ ይህን ነገር ለአንድ ቀልደኛ ጓደኛዬ ስነግረው ምን ቢለኝ ጥሩ ነው፡- “ ‹ለልጅ ይታየዋል› ይባል የለ፤ ልጆቹ ዘመኑ ሌባ የበዛበት እንደሆነ ስለገባቸው እኮ ነው!” አላለም ! እናንተዬ፤ አንዳንድ ሰው ግን እንዴት እንዴት ነው የሚናገረው ባካችሁ! (እኔ እዚህ ላይ ምንም አስተያየት አለመስጠቴን ግን ልብ በሉልኝ )… እንግዲህ የዛሬን በዚህ አብቅቼ፣ የሳምንት ሰው ይበለን በማለት ልሰናበታችሁ ነው፡፡
ቸር ሰንብቱልኝማ
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ