የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ለግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ምርታማነት ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለፀ

የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ለግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ምርታማነት ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገለፀ

የአርሶአደር ማሰልጠኛ ማዕከላት ለግብርና ቴክኖሎጂ ሽግግርና ምርታማነት ያላቸው ድርሻ ከፍተኛ በመሆኑ ሊጠናከሩ እንደሚገባ ተገልጿል፡፡

በባስኬቶ ዞን በላስካ ዙሪያ ወረዳ በጋርባያ ቀበሌ በምግብ ሥርዓት መቋቋም ፕሮግራም በጀት ድጋፍ የተገነባው ዘመናዊ የአርሶአደሮች ማሰልጠኛ ማዕከል ተመርቆ ለአገልግሎት በቅቷል።

የላስካ ዙሪያ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ቡቦ በዙሪያ ወረዳው 4 ቀበሊያት ሞዴል የአርሶአደር ማሰልጠኛዎች ተገንብተው ወደ ተግባር መግባታቸውን ጠቁመዋል።

ማዕከሉ ከሥርዐተ ምግብ ፕሮግራም በተገኘ 6 ነጥብ 4 ሚሊዮን ብር መገንባቱን ገልፀው፤ የግብርና ባለሙያዎች ተመድበው ለአርሶአደሩ የቅርብ ክትትልና የተግባር ስልጠና እንዲሰጡ ምቹ ሁኔታ እንደሚፈጥር አመላክተዋል።

የላስካ ዙሪያ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ክፈለው በለጠ በበኩላቸው፤ መንግስት የግብርናውን ዘርፍ ለማዘመን በትኩረት እየሰራ መሆኑን አንስተው፤ ማሰልጠኛ ማዕከሉ የአካባቢው አርሶ አደሮች የብልጽግና ጉዞ ማሳለጫ ሞተር መሆኑን ጠቁመዋል።

የባስኬቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ኢንጅነር በዛብህ ገበየሁ፤ ማዕከሉ ለአርሶአደሩ የዕውቀት ሽግግር የሚደረግበት ቁልፍ የልማት ማዕከል መሆኑን ተናግረዋል፡፡

አርሶአደሩ ከባህላዊ አሰራር ወጥቶ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም የምግብ ዋስትናውን እንዲያረጋግጥ የዞኑ አስተዳደር አስፈላጊውን ድጋፍ አጠናክሮ እንደሚቀጥል ገልፀዋል፡፡

በመርሃ-ግብሩ ላይ የተገኙ አርሶአደሮች በሰጡት አስተያየት፤ የማሰልጠኛ ማዕከሉ በመገንባቱ መደሰታቸውን ገልጸው፤ የሚጠበቅባቸውን ሥራ በመሥራት ውጤታማ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን