መሬት ውስን የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ በመምራትና ከብክነት በመጠበቅ ቀጣይነት ያለዉን ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ

መሬት ውስን የተፈጥሮ ሀብት በመሆኑ በአግባቡ በመምራትና ከብክነት በመጠበቅ ቀጣይነት ያለዉን ልማት ማረጋገጥ እንደሚገባ ተገለፀ
‎
‎በጌዴኦ ዞን በይርጋጨፌ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት አመት እቅድ ዙሪያ የንቅናቄና ግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ ተካሂዷል።
‎
‎የይርጋጨፌ ከተማ ከንቲባ አቶ ብዙአየሁ ታደሰ፤ መሬት የሁሉም ነገር መሠረትና ውድ ሀብት መሆኑን ገልፀው ከተማችን ከመሬት አስተዳደር አንፃር 94 በመቶ ህጋዊ አድርጎ በመጠቀም በክልል ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው ቢሆንም መቶ በመቶ ተግባራዊ ለማድረግ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል።
‎
‎የጌዴኦ ዞን መሬት አስተዳደር መምሪያ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ ጥላሁን በበኩላቸው፤ መሬት ውስን ሀብት ቢሆንም የኢኮኖሚ ምንጭና የሀገሪቱ እድገት መሠረት ስለሆነ በአግባቡ በመጠቀም ቀጣይነት ያለውን ልማት ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል።
‎
‎የይርጋጨፌ ከተማ ከመሬት አጠቃቀም አንፃር በዞንም ሆነ በክልል ደረጃ ዕውቅና የተሰጠው ተቋም መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ይህንን ወደ ተሻለ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ቅንጅታዊ አሰራሮችን አጠናክሮ ማስቀጠልና ህገ-ወጥነትን መከላከል ላይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ ተናግረዋል።
‎
‎የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም እና የ2019 በጀት አመት እቅድ ሰነድ በይርጋጨፌ ከተማ መሬት አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ባህሩ ማሞ ቀርቦ ውይይት ተደርጎበታል።
‎
‎አቶ ባህሩ ማሞ እንደተናገሩት፤ መሬት የሀገሪቱ ዋነኛ ሀብት እንደመሆኑ መሬትን በአግባቡ መያዝና መጠቀም ያስፈልጋል።
‎
‎ዘጋቢ: ባዩሽ ኢሳያስ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን