የአራት ወራት ቡድንን ከሰባት ዓመት ቡድን ጋር ማወዳደር አይቻልም – ኤንዞ ማሬስካ
የማንቸስተር ሲቲ አሠልጣኝ ኤንዞ ማሬስካ ቡድናቸው አሁን ላይ በሚገኝበት የቡድን ግንባታ ምክንያት በፕሪሚየር ሊግ የዋንጫ ተፎካካሪነት ከአርሰናል ጋር ማነጻጸር እንደማይገባ አስገንዝበዋል።
ለእሁዱ ጨዋታ ዋዜማ ላይ ሆነው በሰጡት አስተያየት፤ የፔፕ ጋርዲዮላን መውጣት ተከትሎ ሲቲ ያለፈበትን ለውጥ እና በሚኬል አርቴታ የሚመራውን የአርሰናል ረጅም የአብሮነት ጊዜ በማነጻጸር ጨዋታውን “የአራት ወር ከሰባት ዓመት“ ፍልሚያ ሲሉ ገልጸውታል።
ማንቸስተር ሲቲ በዚህ ዓመት ለሁለት ወር ተኩል ያህል የሊጉን መሪነት ይዞ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ቡድኑ በመጨረሻዎቹ አራት የሊግ ጨዋታዎች ድል ማስመዝገብ ባለመቻሉ እና በሁሉም ውድድሮች ካደረጋቸው ሰባት ጨዋታዎች ሁለቱን ብቻ በማሸነፉ ከመሪው አርሰናል በስድስት ነጥቦች ልዩነት ወደ ኋላ ቀርቷል።
የመጀመሪያዎቹ ድሎች በፈጠሩት ከፍተኛ ግምት ምክንያት በቡድኑ ውስጥ ያለው የሽግግር ሂደት በብዙዎች ዘንድ ተዘንግቶ እንደነበር ማሬስካ ጠቅሰዋል።
ቡድኑ በሊጉ ሰባት፣ በቻምፒዮንስ ሊግ እንዲሁ ተከታታይ ጨዋታዎችን ማሸነፉ ሰዎች ሽግግር የለም ብለው እንዲያስቡ እንዳደረገ ገልጸዋል።
በቡድኑ ወቅታዊ አቋም ላይ ምንም ዓይነት ድንጋጤ እንደሌላቸው የገለጹት ማሬስካ፤ ጨዋታዎችን የማሸነፍ ግዴታ እንዳለባቸው ቢያውቁም ሁኔታውን በተረጋጋ መንፈስ እያዩት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በነገው ዕለት አርሰናል እና ማንቸስተር ሲቲ የሚያደርጉት ይህ ተጠባቂ ጨዋታ፤ የአጭር ጊዜ የግንባታ ሂደት እና የረጅም ጊዜ የቡድን ቅንጅት የሚፋጠጡበት ወሳኝ መርሐ ግብር ይሆናል።
ጨዋታው በነገው ዕለት ምሽት 1 ሰዓት ከ30 ላይ በኤምሬትስ ስታዲየም የሚካሄድ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ከወራጅ ቀጣና ለመውጣት የሚደረግ ትንቅንቅ
ማንቸስተር ዩናይትድ የአምበሉን ብሩኖ ፈርናንዴዝ ውል በአንድ ዓመት አራዘመ
የዴክላን ራይስ ትልቁ ውርርድ