በዓሉ በሆሳዕና ከተማ በደማቅ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች እየተከበረ ይገኛል

በዓሉ በሆሳዕና ከተማ በደማቅ ሃይማኖታዊ ትውፊቶች እየተከበረ ይገኛል

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዲያና ስልጤ ሀገረ ስብከት ምክትል ስራ አስኪያጅ መጋቤ ጥበብ ቀሲስ ወርቁ ተክሌ እንደገለፁት፤ የመስቀል ደመራ በዓል ክርስቶስ ተሰቅሎበት የነበረን መስቀል አይሁዶች በቅናት ቀብረውት ለዘመናት ቆይቶ ንግስት እሌኒ በደመራ ጭስ ጥቆማ መስቀሉ የተቀበረበትን ማግኘቷን አብነት በማድረግ የሚከበር ነው።

በዓሉ በዓለም የሳይንስና ባህል ሙዝየም “ዩኔስኮ” በማይዳሰስ ቅርስነት በመመዝገብ ለሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻነት ከማገልገልም በላይ በርካታ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳዎች ያሉት ስለመሆኑ ገልፀዋል።

በዓሉ እንደ ደመራው ችቦ ህብረት ሁሉ የህዝብ ለህዝብ ትስስርን ከማጎልበት ረገድ ጉልህ ሚና ያለው ነው ብለዋል።

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በዓሉ በየዓመቱ መስከረም 16 ቀን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ክዋኔዎች ታጅቦ የሚከበር እንደሆነ በመጠቆም፤ በዓላት ሲከበሩ ሁሉም ያለሃይማኖት ልዩነት ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሠላም ዘብ በመቆም ብሎም የተቸገሩ ወገኖችን በመደገፍ ሊሆን ይገባል ሲሉ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በበዓሉ ላይ የተገኙ የእምነቱ ተከታዮችም በዓሉን በታላቅ ሃይማኖታዊ ድምቀት እያከበሩ እንደሚገኙ ገልፀዋል።

በበዓሉ የሀዲያና ስልጤ ሀገረስብከት ሊቀጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ ተገኝተው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ የሰጡ ሲሆን የሀገረ ስብከቱን ዋና ስራ አስኪያጅ መልአከ ሕይወት ቀሲስ ንጉሴ ባወቀን ጨምሮ ከተለያዩ አካባቢዎች የተውጣጡ ምዕመናንና ተጋበዥ እንግዶች ተገኝተው በዓሉን በድምቀት እያከበሩ ነው።

ዘጋቢ: አማኑኤል አጤቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን