የስኬት ዋንኛው ቁልፍ ፍላጐት ነው
በቤተልሔም አበበ
የልጆችን አካላዊና ስነ ልቦናዊ ጉዳቶችን በመቀነስ ረገድ ወላጆች አዎንታዊ ሚና ሊጫወቱ ይገባል፡፡ በተለይ በጨቅላ ዕድሜ የሚገኙት ይበልጥ ትኩረት ያሻቸዋል፡፡
ለዚህም ምክንያቱ ኑሮን ለማሸነፍ በሚደረገው ትግል ልጆች ተጎጂ ስለሚሆኑ ነው፡፡ አብዛኞች ወላጆች ግና ልጆቻቸውን በቅርበት ለመከታተል እና ለመጠበቅ አይችሉም፡፡
ወላጆች የቤተሰብን ሀላፊነት ለመወጣት በተለያዩ መስኮች ተሰማርተው ስለሚሰሩ አብላጫውን ጊዜ ከቤት ውጪ ያሳልፋሉ። ልጆችም በዚህን ጊዜ ከሞግዚቶቻቸው ጋር እንዲውሉ ይደረጋል፡፡
በተለይ በለጋ እድሜ የሚገኙ ህጻናት በአግባቡ እንክብካቤ ካልተደረገላቸው በአካላቸው ላይ ጉዳት ስለሚደርስ ለችግሮች ይጋለጣሉ፡፡
ስለሆነም ወላጆች ከስራ ወደ ቤት ሲመለሱ የልጆችን ሰውነት በመደባበስ፣ በመነካካት የጤናቸውን ሁኔታ በማረጋገጥ በኩል ልምዳቸው ምን ያህል ነው ሲባል ደግሞ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡
ወጣት ወንጌላዊት ታምሩ ትባላለች። የተወለደችው በኦሮሚያ ክልል ነው፡፡
ወላጆቿ ከተወለደችበት አካባቢ በመዘዋወር ኑሯቸውን ጌዴኦ ዞን ይርጋ ጨፌ ከተማ አድርገው ዕድገቷም በዚያ ከተማ ሆነ፡፡
ስትወለድ ጤናማ ሆና እንደነበረች ታስታውሳለች፡፡ ይሁን እንጂ ወላጅ እናቷ እንዲጠብቋት ለዘመድ ልጆች ትተው ስራ በሄዱበት ጊዜ በመውደቋ ለአካል ጉዳተኝነት እንደተዳረገች ታስታውሳለች፡፡
የህጻኗ መውደቅ ለጊዜው ለወላጆቿ አለመነገሩ ደግሞ ችግሩን የከፋ አድርጎታል፡፡
ውሎ ሲያድር እየታመመች ስለነበረ ወደ ህክምና ተቋም በመውሰድ ለረጅም ጊዜ ስትረዳም ቆየች፡፡
ከህክምናው ባሻገር ቀና ማለት የጀመርኩት በባህላዊ ወጌሻ ነው ስትልም ነግራናለች፡፡
የባህላዊ ወጌሻ ስራ የሚሰሩ አካላት እንደ ስራቸው እና እንደ ውለታቸው ብዙም ያልተነገረላቸው ባለሙያዎች እንደሆኑም ምስክርነቷን ሰጥታለች፡፡ የሚሰጡት አገልግሎት ከስብራት ጥገና እስከ ህይወት ማትረፍ ነው፡፡
ከዚህ ቀደም የባህል ሀኪሞች በመንግስት በመታገዝ አዳዲስ ስልጠናዎችን እንዲያገኙ እና እራሳቸውን እንዲያሻሽሉ የሚደረግበት አግባብ ነበር፡፡ አሁን ላይ ትኩረት እየተሰጠው አይደለም፡፡
ወጣቷ ትምህርቷን እስከ አስረኛ ክፍል ተከታትላለች፡፡ ነገር ግን ትምህርቷን ለማጠናቀቅ ምኞት እና ዓላማ ቢኖራትም ህልሟን ለማሳካት አልቻለችም፡፡
ወላጅ አባቷ ከሞቱ በኋላ ኑሮ እንደ ቀድሞ የተደላደለ አልሆነላትም፡፡ በዚህም ሰፈር ለሰፈር እየተንቀሳቀሰች የሴቶችን ጸጉር ሽሩባ በመስራት የገቢ ምንጭ መፍጠር እንደጀመረች አጫውታናለች፡፡
የኑሮ ውጣ ውረዱ ከአካል ጉዳቷ ጋር በመሆን ትልቅ የስነ-ልቦና ጫና ፈጥሮባት እንደነበረም ነው ወንጌላዊት የተናገረችው። ነገር ግን እራሷን ለመለወጥ በምታደርገው ጥረት የአካል እንጂ የአእምሮ ጉዳተኛ አለመሆኗን ያሳየችው፡፡ እቀየራለሁ፣ እችላለሁ የሚል ተስፋን ያነገበች እንስት ስለመሆኗ ጥንካሬዎቿ ማሳያ ናቸው፡፡
በየአካባቢው እየተንቀሳቀሰች የጸጉር ስራዎችን በመስራት እራሷን ካስተዋወቀች እና ሙያዋን ካሳደገች በኋላ በጸጉር ቤት እንደተቀጠረች አጫወተችን፡፡
ጸጉር ቤት ትቀጠር እንጂ በቂ ገንዘብ አይከፈላትም፡፡ ታገኝ የነበረው ከሰራችው ሹሩባ ክፍያ ግማሹን ብር ነበር፡፡ ያም ሆኖ ከምታገኘው ገንዘብ በመቆጠብ ለሁለት አመት እንዳጠራቀመች ትናገራለች፡፡
በመንግስት የተፈጠሩ ምቹ አጋጣሚዎችን በመጠቀም በማህበር በመደራጀቷ ሼድ የማግኘት ዕድል አጋጥሟታል፡፡
በሰው ቤት ስትሰራ ያዳበረችውን የጸጉር ሙያ በግሏ በመክፈት ከሹርባ ባለፈ የተለያዩ የመገልገያ ቁሳቁሶችን በመግዛት አገልግሎት መስጠት ጀመረች፡፡
ከአካል ጉዳተኝነቷ ጋር በተያያዘ ስላጋጠሟት አንዳንድ ማህበራዊ ጫናዎችን ስትናገር፡-
“ሰዎች በመንገድ ላይ ስሄድ የእግሬን ጉዳት በመመልከት ሲያዝኑልኝ ይሰማኛል። ለምን? እላለሁ፡፡ አካል ጉዳተኛ ብሆንም እንኳን እንደ ማንኛውም ጤናማ ሰው ሁለት ሰራተኛ በጸጉር ቤቴ ቀጥሬ እያሰራሁ ደሞዝ በመክፈል ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር ችያለሁ፡፡
እንደ ወጣቷ አስተያየት አንዳንድ ጊዜ አካል ጉዳተኛ ሆነን ከሌላው ነጥረን ስንወጣ የሰዎች እይታ ወደኋላ እድንመለስ የሚያደርግ በመሆኑ ለነቀፌታዎች ቦታ መስጠት ተገቢ አለመሆኑንም ትናገራለች፡፡
በየቤቱ በርካታ አካል ጉዳት ያለባቸው ሴቶች እና ወንዶች በቅድሚያ ማድረግ ያለባቸውን አካል ጉዳተኝነት አለመቻል አይደለም ብለው ማመን ያለባቸው፡፡ ስነ ልቦናችንን በማጠንከር ከስኬት ማማ ላይ መድረስ ይቻላል የሚለው የህይወት መርሆዬ ነው ትላለች ወንጌላዊት፡፡
“አካል ጉዳተኞች ብዙን ጊዜ የፍቅር ህይወት እና ታሪክ እንደማያስፈልጋቸው ተደርጎ ይወሰዳል ትላለች” ወጣት ወንጌላዊት ግን እንደማንኛውም ሰው የፍቅር ታሪክ ያላት እንስት ናት፡፡ ከፍቅር አጋሯ ጋር ለረጅም ጊዜ አብረው እንደቆዩም አጫውታናለች፡- “አካል ጉዳተኛ በመሆኔ የፍቅር አጋር አላጣሁም ምክንያቱም ከማንኛውም ሰው እኩል ሰርቼ መኖር በመቻሌ ነው” የሚል አስተያየት አላት፡፡ በቅርቡ ከፍቅር አጋርዋ ጋር ትዳር እንደምትመሰርትም አጫውታናለች፡፡
የስኬት ዋንኛው ቁልፍ ፍላጎት በመሆኑ አካል ጉዳተኛ መሆን ምንም አይነት ተጽዕኖ አያስከትልም ስትልም ነው ወጣት ወንጌላዊት የገለጸችው፡፡
ሰፊ ራዕይ ያላት ከመሆኗ የተነሳ በጸጉር ሙያ ላይ ብቻ እየሰራች መቆየት እንደማትፈልግና ወደ ፊት የሸቀጣሸቀጥ ማከፋፈያ ሱቅ ለመክፈት እያሰበችና ለዚህም ከምታገኘው ገቢ ላይ እየቆጠበች መሆኗን ገልጻልናለች፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ