ክፍል ሁለት
በቦጋለ ወልዴ
ውድ የንጋት ጋዜጣ አንባቢዎቻችን እንደምን ከርማችኋል? በባለፈው ሣምንት የህትመት ገፃችን (በኪነጥበብ አምድ) የሠፈረው በኑሮ ውጣ ውረዳችን በምንተጋው የስኬት ጉዟችን በደንቃራ አስተሳሰብ ሳቢያ ደስተኛ አለመሆን የሚፈጠርባቸው ጥቂት ሰበብ አሰባቦችን ዋቢ በመጥቀስ ከዓምዳችን ገፅ የሰፈረውን እንዳጣጣማችሁት በማመን፡-
ዛሬም “The cosmic energizer Miracle power of the universe” “የአሸናፊነት ስነ ልቦና” በሚል በመተርጐም ለንባብ ያዘጋጀልን የሀገሬን ሰው ውድ ብዙአየሁ ገበየሁ ለዚሁ ፅሑፍ ዋቢዬ ነውና በአንባቢያንና በዝግጅት ክፍሉ ስም እያመሰገንኩኝ ግብዣዬ እንደሚከተለው ይገኛል፤ በንባብ እንዝለቅ፡፡
እንቅፋት በሌለበት መደናቀፍ፡-
ከዓመታት በፊት አንድ ጓደኛዬ የወደቀ ግንድ ሲያጋጥመው እየተፈናጠረ ስለሚዘል ፈረስ ታሪክ አጫውቶኝ ነበር። ይህ ፈረስ የወደቀ ግንድ ሲያይ የሚዘለው መጀመሪያ ላይ ፈረሱ ከወደቀው ግንድ አጠገብ እባብ አይቶ ስለነበርና በዚያም ከፍተኛ ፍርሃት ስለተሰማው ነው፡፡
ይህንንም ተከትሎ ፈረሱ የወደቀ ግንድ ባጋጠመው ቁጥር ይዘላል፡፡ የፈረሱ ባለቤትም ያወርድና እንቅፋቱን አንስቶ ጉዞውን ይቀጥላል፡፡ ይህን ግን ምክንያቱ አልተረዳውም፤ ሊረደውም አልቻለም፡ ፡ የሚገርመው ነገር ይህ ፈረስ ለቀጣዮቹ 25 ዓመታት እንቅፋት ይገጥመው በነበረው ሥፍራ ላይ ሲደርስ ግስጋሴውን ትቶ እያናፋ ዘለል ዘለል የማለቱን ነገር አለማቋረጡ ነበር፡፡ ፈረሱ ይህን ያደርግ የነበረው ግን የቀድሞው እንቅፋት ስር የነበረው እባብ ትዝ እያለው ነበር፡፡
በአእምሮህ ከምትፈጥረው ኃሳብ በስተቀር ለደስታህ አንዳች እንቅፋት የለም፡፡
ፍርሃት ወይንም ጭንቀት ወደ ኋላ ጎትተውሃል? ፍርሃት በጭንቅላትህ ውስጥ የምትፈጥረው ሃሳብ ነው። በአሁኗ ቅፅበት እርሱን ስኬታማ ልትሆን እንደምትችልና ችግሮችህን ሁሉ በስኬት መለወጥ እንደምትችል በማመን ልትተካው ትችላለህ፡፡
ለፅሁፌ ዋቢዬ የሆነው ተርጓሚ ብዙአየሁ አያሌው እንደዚህም ይለናል፡-
የንግድ ሥራ አልሆንልህ ብሎት የነበረን አንድ ሰው አውቅ ነበር፡፡ ይህ ሰው በወቅቱ በነበረን ውይይት እንዲህ ነበር ያለኝ፡፡ “ከዚህ በፊት በርካታ ስህተቶችን ሰርቻለሁ፡፡ ነገር ግን፤ ከእነዚህ ስህተቶቼ ትምህርቶችን ቀስሜያለሁ፡፡
እናም እንደገና ተመልሼ ንግድ ውስጥ በመግባት ስኬትን እጐናፀፋለሁ ይህ ሰው አእምሮው ውስጥ የነበረውን እንቅፋት ፊት ለፊት ተጋፈጠው፡፡ ከንግዱ ዓለም በኪሳራ ለመውጣቱ እንቅፋቶቹን አላማረረም፡፡ ከዚያ ይልቅ ስህተቶቹን ለስኬት ተጠቀመባቸው እንጂ፡፡ እናም እንደገና ወደ ቀድሞ ንግዱ እንዲመለስ ያደረገው ውስጣዊ ኃይል በመሆኑ የተነሣ ሁሉንም የፍርሃትና የብስጭት ሃሳቦችን አስወገደ፡፡ በራስህም ስታምን ደስተኛና ስኬታማ ትሆናለህ” ብሎናል፡፡
ደስተኞቹ ሰዎች
ደስተኛ ሰው ማለት ጠንካራ ጐኑን ተረድቶ ጠንካራውን የሚያጐላ ተግባር የሚፈፅም ሰው ማለት ነው፡፡ ደስተኛና መልካምነት ይደጋገፋሉ፡፡
ምርጦቹ ደስተኞች ብቻ አይደሉም። ነገር ግን፤ ደስተኞች ስኬታማ ህይወትን በመኖር ምርጥ የሆኑት ናቸው፡፡
የአንተ ከፍታና ምርጡ እግዚአብሔር ነው፡፡ በመሆኑም የእግዚአብሔርን ፍቅር፣ ብርሃን፣ አንድነትና ውበት ስትገልፅ ዛሬ በዓለም ላይ ደስተኛ ከሆኑት ሰዎች መካከል አንዱ ትሆናለህ፡፡
ኤፒክቲተስ የተባለ የግሪክ ፈላስፋ እንዲህ ብሎ ነበር፡፡ “በአእምሮህ ለሰላምና ለደስታ ያለው መንገድ አንድ ብቻ ነው። በመሆኑም ዘወትር ማለዳ ከእንቅልፍህ ስትነቃ አንስቶ ምሽት ወደ መኝታህ እስክትሄድ ድረስ ለቁሳዊ ነገሮች ትኩረት ነፍገህ መንገድህን በእግዚአብሔር አቅና” በማለት መንፈሳዊ ምክሩን ለግሶናል፡፡
የአሸናፊ ሥነ-ልቦና የተሰኘችው መጽሐፍ ተርጓሚ አንኳር አንኳር የመጽሐፏ ገፆች ከተካተቱት ውስጥም እንደሚከተለው በማሰናዳት ቁምነገሮቹን ልብ እንል ዘንድ በቀለሙ ነቅሷቸዋል፡፡
የማጠቃለያ ነጥቦች፡-
• ማንኛውንም ሽንፈት ወደ ድል መለወጥ ይቻልሃል፡፡ በውስጠ ህሊናህ ታላቅ ኃይል አማካኝነትም የልብህ ፍላጐት ምን እንደሆነ ትገነዘባለህ፡፡ (በውስጠ ህሊና መንፈሳዊ ህግጋት) የሚታመን ሁሉ ደስተኛ ይሆናል ማለት ይኸው ነው፡፡
• ማለዳ ከእንቅልፍህ ስትነቃ ለራስህ እንዲህ በል ዛሬ ደስተኛ ለመሆን መርጫለሁ ይህን አስተሳሰብ በፍቅር፣ በህይወትና በፍላጐት ስትደግፈው ደስታን መርጠሃል ማለት ነው፡፡
• በየዕለቱ ለየበረከቶችህ ሁሉ ምስጋና አቅርብ፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ለአጠቃላይ ቤተሰብ አባላትህ፣ ለሥራ ባልደረቦችህ እና ለሰው ልጆች ሁሉ ሰላም፣ ደስታና ብልፅግና ይሆን ዘንድ ፀልይ፡፡
• ደስተኛ ለመሆን ከልብህ መፈለግ አለብህ፡፡ ያለ መሻት አንዳችም ነገር እውን አይሆንም፡፡ መሻት በእምነትና በምናባዊ እይታ ላይ የተንጠለጠለ ብርቱ ምኞት ነው፡፡ የፍላጐትህን እውን መሆን በዓይነህ ህሊናህ አሻግረህ ተመልክተው። እውንነቱ ይሰማ ሲያልፍም እንዲያው የዚያን ጊዜ ደስተኝነት የፀሎትህ መልስ ሆኖ ይመጣል፡፡
• ደስታ በገንዘብ አይገዛም። ለዚያም ነው በርካታ ሚሊኒየሮች ደስታ ርቋቸው የሚስተዋለው፡፡ ግን ደግሞ ደስተኛ ባለፀጋዎች እንዳሉ መዘንጋትም የለበትም፡፡ የተወሰኑ ባለትዳሮች ደስተኞች ሲሆኑ የተወሰኑት ደግሞ ደስታ የራቃቸው ናቸው፡፡ ብቸኝነት አንዳንዱን ደስተኛ ሲያደርገው ሌሎችን ደግሞ በትካዜና በቁዘማ ዓለም እንዲኖሩ ያደርጋቸዋል። ይህ የሚያሳየው ደስታ የሚፈጠረው በስሜቶቻችንና በሃሳቦቻችን ውስጥ መሆኑን ነው፡፡
• ደስተኛ ሰው የሚሰጡትን ምጡቅነት አጉልቶ የሚያሳይ ነው፡፡ የእግዚአብሔር መንግስት ውስጣዊ ነችና፤ በውስጣችን ያለው ከፍታና ታላቅነት እግዚአብሔር ነው፡፡
ውድ አንባቢያን፤ የአሸናፊነት ሥነ ልቦናን የተጐናፀፈ ሰው ከስኬታማነት ጐራ የማይሰለፍበት አንዳች ምክንያት የለምና ካለፈው ሣምንት ዕትምና ከዚህችኛዋ የኪነ- ጥበብ ዓምድ ጥንቅር ራሳችንን እንዴት ቃኝተነው ይሆን?
በቸር እንሰንብት!!
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው