ክርስቲያኖ ሮናልዶ እና የዓለም ዋንጫ
ለአብዛኛዎቹ እግር ኳስ ተጫዋቾች የዓለም ዋንጫ የከፍታ ጥግ ነው።
ለክርስቲያኖ ሮናልዶ ግን፣ ለሁለት አስርት ዓመታት የዘለቀው ይህ መድረክ የጀግንነት ማረጋገጫ ሳይሆን፣ እንደ “የማይሳካለት ምኞት “ሆኖበት ቆይቷል።
እ.ኤ.አ በ2010 የዓለም ዋንጫ ዋዜማ፣ “ታሪክህን ጻፍ” (Write The Future) በሚል መሪ ቃል በተሰራው ታዋቂው የናይኪ ማስታወቂያ ላይ፣ ሮናልዶ በዓለም ዋንጫ ፍጹም ስኬታማ ሆኖ ሲያስብ ተስሎ ነበር።
ማስታወቂያው በዚያን ጊዜ የነበረውን ህልም ያንፀባርቅ ነበር፤ ነገር ግን እውነታው ከማስታወቂያው ፈጽሞ የተለየ ሆኖ አረፈ።
ከ2006 እስከ 2026 ባሉት ስድስት የዓለም ዋንጫዎች ሮናልዶ ብዙ ውጣ ውረዶችን አሳልፏል።
በ2006 ጀርመን ላይ የነበረው የዓለም ዋንጫ ጉዞው ለሮናልዶ ተስፋ ሰጪ ነበር። በሩብ ፍጻሜው እንግሊዝን ሲያሸንፉ ያስቆጠረው ወሳኝ ፍጹም ቅጣት ምት በብዙዎች ትውስታ ውስጥ አለ።
በ2018 በስፔን ላይ ያስቆጠረው አስደናቂ ሀትሪክ፣ እና በቅርቡ በክሮኤሽያ ላይ ያስቆጠራት የጥሎ ማለፍ ጎል የዓለም ዋንጫ ጉዞው ጥቂት ብሩህ ነጥቦች ናቸው።
ከነዚያ ውጪ ግን በዓለም ዋንጫው ላይ ታሪኩ የጨለመ ነበር። በ2010 አሳዛኝ ሽንፈት፣ በ2014 በጉልበት ጉዳት የታጀበ እና ዝቅተኛ ውጤት ማስመዝገብ፣ በ2018 የነበረው ከፍተኛ ጉጉት… ሁሉም የሮናልዶን እና የፖርቹጋልን ህልም ማሳካት አልቻሉም።
በ2022 በሞሮኮ ከተሸነፉ በኋላ ባለቀሰው እንባ እና ትናንት ምሽት በስፔን ሽንፈት የዓለም ዋንጫ ጉዞው በይፋ ተጠናቋል።
በ41 ዓመቱ በታሪኩ የመጨረሻ የዓለም ዋንጫ ላይ፣ በሜዳው ላይ የፈሰሰው የዓይን እንባ በዘመኑ የነበረውን የብስጭት እና የትግል ማጠቃለያ ያሳያል።
ብዙዎች “ክርስቲያኖ የዓለም ዋንጫን ካላነሳህ ምርጥ ተጫዋች አይደለም” የሚል መከራከሪያ ያቀርባሉ።
ሆኖም ሮናልዶ ራሱ ከፒርስ ሞርጋን ጋር በነበረው ቃለመጠይቅ እንደተናገረው”ዓለም ዋንጫን ማሸነፍ ወይም አለማሸነፍ በታሪክ ውስጥ ያለኝን ስም አይቀይረውም” ሲል ገልጿል።
የናይኪው ማስታወቂያ ሮናልዶ ዓለም ዋንጫን በማንሳት ታሪክ እንደሚጽፍ ተንብዮ ነበር። እውነታው ግን ከዚህ ይበልጣል። ሮናልዶ ታሪኩን የጻፈው በዓለም ዋንጫ መድረክ ብቻ አይደለም፤ ይልቁንም በሁለት አስርት ዓመታት የልፋት፣ የቁርጠኝነት እና የብቃት ማሳያ ነው።
የዓለም ዋንጫ ለእርሱ ያልተሳካለት የፍቅር ታሪክ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን ይህ “የጎደለ እትም” የእግር ኳስ ታላቅነቱን ሊቀንስ አይችልም።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ የሜዳው ጀግና ሆኖ የተሰናበተበት መንገድ፣ ታሪኩ ቀድሞ የተጻፈ እና የማይደመሰስ መሆኑን ያስታውሰናል።
ያለ ጥርጥር፣ ሮናልዶ በዓለም ዋንጫ ሳይሳካለት ቢቀርም፣ በእግር ኳስ ዓለም ግን የማይበገረው የዘመናችን ኮከብ ሆኖ ይኖራል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ሲዳማ ቡና የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ አነሳ
የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በሲዳማ ቡና አሸናፊነት ተጠናቀቀ
ማንቸስተር ዩናይትድ የቼልሲውን አማካይ አንድሬይ ሳንቶስን ለማስፈረም ፍላጎት አሳየ