በዱራሜ ከተማ አስተዳደር የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን አንዳንድ የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ተናገሩ

በዱራሜ ከተማ አስተዳደር የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን አንዳንድ የሆስፒታሉ ተገልጋዮች ተናገሩ

በከምባታ ዞን የዱራሜ ከተማ አስተዳደር የዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታልን የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ እየተሰራ መሆኑም ተገልጿል፡፡

በዶክተር ቦጋለች ገብሬ መታሰቢያ አጠቃላይ ሆስፒታል በዘመናዊ የህክምና መሣሪያዎችና በብቁ የህክምና ባለሙያዎች በመታገዝ ደረጃቸውን የጠበቁ አገልግሎቶችን እየሰጠ መሆኑን ከሆስፒታሉ ያገኝነው መረጃ ያመለክታል።

የሆስፒታሉ ዋና ስራ አስኪያጅ ዶ/ር ደረበ ዮሐንስ እንደገለጹት፤ ከካርድ ክፍል ጀምሮ የእናቶች ወሊድ አገልግሎትን ጨምሮ የድንገተኛ፣ ተመላላሽ፣ ተኝቶ ህክምና አገልግሎት በሆስፒታሉ ስፔሻሊስት ሀኪሞች በተሟላ የላቦራቶሪ ምርመራ እየሰጠ ነው።

በውስን የህክምና ዘርፎች የጀመረውን የአገልግሎት አሰጣጥ ሂደት ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሰፋ የሆስፒታሉን የግንባታ አቅም በማስፋፋት በዘመናዊ መሳሪያዎች እየታገዘ የህክምና አገልግሎት እየሰጠ እንደሚገኝ ተጠቁሟል።

ባሳለፍነው የበጀት ዓመት በሆስፒታሉ ከምባታ ዞንን ጨምሮ ከተለያዩ አጎራባች ዞኖች ለሚመጡ ከ2 ሚሊየን በላይ ለሆነ ማህበረሰብ ህክምና አገልግሎት መሰጠቱንም ዶክተር ደረበ አመልክተዋል::

የእናቶችና ህፃናትን ጤና ለማሻሻል በተደረገው ጥረት በርካታ እናቶች በሆስፒታሉ የወሊድ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን አመላክተዋል::

አሁን ላይ ለተገልጋዮች በሲቲ ስካን የታገዘ ህክምና እየተሰጠ መሆኑን ጠቅሰዋል::

በቀጣይ የታካሚዎችን እንግልት ለማስቀረት የአንጎል ቀዶ ህክምና እና የፌስቱላ ህክምና አገልግሎት ለማስጀመር ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በትኩረት እየተሰራ መሆኑም ዶ/ር ደረበ አሳውቀዋል።

የአገልግሎት ጥራትና ውጤታማነትን በማሳደግ በስፔሻሊስት ሀክሞች እንደ ሀገር ውስንነት ያለበትን የአጥንት ቀዶ ህክምና እና የቆዳ ህክምና መስጠት መቻሉን የገለጹት ዶ/ር ደረበ በቀጣይ የሆስፒታሉን አቅም ይበልጥ በማጎልበት የሜዲካል ቱሪዝም ማዕከል ለማድረግ የኦክሰጅን ማምረቻና ሌሎች ቁሳቁሶች በተገቢው መሟላታቸውን አመላክተዋል።

በ2019 በጀት ዓመት የመረጃ አያያዝ ስርዓት ዘመናዊ እንዲሆን ሁሉንም አገልግሎቶች ዲጂታል በማድረግ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓትን መዘመን መቻሉን ዶክተር ደረበ ጠቁመዋል:።

ከመድኃኒት አቅርቦት አኳያም በሆስፒታሉ የሚስተዋሉ የመድኃኒት እጥረቶችን ለመቅረፍ በርካታ ጥረቶች እየተደረገ እንደሆነ ዶክተር ደረበ ጠቅሰዋል።

በሆስፒታሉ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ባለሙያዎች በበኩላቸው የምሳ ሰዓትን ጨምሮ ቀን እና ማታ እየገቡ ለታካሚዎች ቀልጣፋ አገልግሎት በመስጠት ሙያዊ ግዴታቸውን በተገቢ እየተወጡ እንደሆነ ጠቅሰዋል።

በሆስፒታሉ ያነጋገርናቸው አንዳንድ ተገልጋዮች እንዳሉት አሁን ላይ በሆስፒታሉ እየተሰጠ ባለው አገልግሎት ደስተኞች መሆናቸውን ገልጸዋል።

ዘጋቢ: በየነ ሰላሙ – ከሆሳዕና ጣቢያችን