ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ሲፋለም አርሰናል ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል

ማንችስተር ዩናይትድ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ሲፋለም አርሰናል ከሜዳው ውጪ ወሳኝ ጨዋታ ይጠብቀዋል

በእንግሊዝ እግር ኳስ ታሪክ ትልቅ ቦታ ያለውና የሊድስ ዩናይትድ እና ማንቸስተር ዩናይትድ ጠንካራ ፉክክር የሚታይበት የሮዝ ደርቢ ዛሬ በሊድስ ዩናይትድ አስተናጋጅነት ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።

በዚህ የውድድር ዘመን አስቸጋሪ ጊዜን እያሳለፈ የሚገኘው ማንችስተር ዩናይትድ፣ ከስድስት የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው አንዱን ብቻ ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ በሻምፒዮንስ ሊግ በአትሌቲኮ ማድሪድ የደረሰበትን ሽንፈት በመርሳት ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ዛሬ ከሜዳው ውጪ ከባድ ፈተና ይጠብቀዋል።

ሊድስ ዩናይትድ በ9 ነጥብ 8ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፤ ማንችስተር ዩናይትድ በበኩሉ በ6 ነጥብ ብቻ 14ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል።

ቀይ ሰይጣኖቹ ፓትሪክ ዶርጉን፣ ቤንጃሚን ሼሽኮን እና ማኑኤል ኡጋርቴን በጉዳት ምክንያት አያገኙም፤ የሉክ ሾው እና ኮቢ ማይኖ በዛሬው ጨዋታ መሰለፍም አጠራጣሪ ሆኗል።

በሌላኛው የሊጉ መርሃ-ግብር ሻምፒዮኑ አርሰናል ከሜዳው ውጪ በሲቲ ግራውንድ ከኖቲንግሀም ፎረስት ጋር ከምሽቱ 12 ሰዓት ከ30 ላይ ይጋጠማል።

መድፈኞቹ ከቅርብ ተቀናቃኛቸው ከማንችስተር ሲቲ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት ወደ ነበረበት 3 ዝቅ ለማድረግ የማሸነፍ ግዴታ አለባቸው።

ሆኖም ከሜዳቸው ውጪ ከሚያደርጉት ጉዞ ቀላል የማይባል ፈተና እንደሚጠብቃቸው ይገመታል።

በአርሰናል በኩል ፒዩሮ ሂንካፒዮ፣ ክሪስቶስ ዞሊስ እና ዊሊያም ሳሊባ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሲሆኑ፤ አማካዩ ማርቲን ዙቢሜንዲ ግን በዛሬው ጨዋታ ሊሰለፍ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል።

በኖቲንግሀም በኩል ሞርጋን ጊብስ ዋይት እና ኒኮላ ሚሊንኮቪች መሰለፋቸው ያልተረጋገጠ ሲሆን፣ ኢጎር ጀሱስ በጉዳት ከጨዋታው ውጪ ሆኗል።

ብራይተን ከ ክርስታል ፓላስ እንዲሁም ቦርንመዝ ከ ሰንደርላንድ ከቀኑ 10 ሰዓት ላይ የሚደረጉ ሌሎች የዛሬ መርሐግብሮች ናቸው።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ