የመደመር መንግስት አሳታፊ የሆነ የልማት ተግባራትን እያከናወነ የህዝብን የመልማት ጥያቄዎች እየመለሰ ይገኛል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን

የመደመር መንግስት አሳታፊ የሆነ የልማት ተግባራትን እያከናወነ የህዝብን የመልማት ጥያቄዎች እየመለሰ ይገኛል – የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልላዊ መንግስት ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን ከዳውሮ ዞን ከተወጣጡ የማህበረሰብ ተወካዮች ጋር በታርጫ ብዘሃ ከተማ ውይይት እየተካሄዱ ይገኛል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር አቶ ፍቅሬ አማን በዚሁ ወቅት እንደተናገሩት፤ የመደመር መንግስት ባለፉት ጊዜያት አሳታፊ የሆነ የልማት ተግባራትን እያከናወነ የህዝብን የመልማት ጥያቄዎች እየመለሰ ነው ብለዋል።

ክልሉ ያለውን እምቅ የተፈጥሮ ጸጋን ወደ ሃብት በመቀየር የሕዝቡን የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በትጋት እየተሰራ ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለውም በየአካባቢው ያለውን ጸጋ በመለየት ለህዝቡ ተጠቃሚነት እንደሚሰራ በአፅንኦት አንስተው፤ መድረኩ የህዝቡን ብልጽግና ለማረጋገጥ አገልጋይ መሆናችንን ለማረጋገጥ የተዘጋጀ ነው ብለዋል።

የዛሬው ውይይት ለነገው ስራችን መነሳሻ በመሆኑ፤ ህዝቡ  ከመደመር መንግስት ጎን በመሆን የተጀመረው ለውጥ እንዲቀጥል አበርክተው የጎላ መሆኑን ገልጸዋል።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ትዕዛዙ ባዩ በበኩላቸው፤ እንደሀገር የተጀመረውን ለውጥ ለማስቀጠልና በተጨባጭ የህዝብን ኑሮ ለማሻሻል በልዩ ትጋት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

በቅርቡ በተከናወነው የመደመር መንግስት ምስረታ ማግስት ለህዝባዊ ውይይት ወደ ዞናችን እንኳን በደህና መጣችሁ ያሉት አስተዳዳሪው፤ የዳውሮ ህዝብ ለዘመናት የህዝብ የጋራ ክልል በመመስረት የመልማት ጥያቄው ምላሽ እንዲያገኝ ሲያደርግ የነበረው ትግል በአዲሱ ክልል ምስረታ ምላሽ ማግኘቱን አስታውሰዋል፡፡

በፓርቲ ኢኒሼቲቪ በዞኑ የተጀመሩ ተግባራት  የህዝብን ተጠቃሚነትና የሰብዓዊ ድጋፍ  በተግባር የተረጋገጡ ውጤት ማምጣታቸውንም ገልፀዋል፡፡

በዞኑ የመንገድ መሠረተ ልማት ችግር እንዲፈታ ለማስቻል የተጀመሩ ፕሮጀክቶች አፈጻጸም በተያዘው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ህዝቡ ለብልፅግና ፓርቲ የሰጠውን አደራ በመረዳት በቀጣይነት በትኩረት እንደሚሰራ አመላክተዋል፡፡

በውይይት መድረኩ ከሚሳተፉ የህብረተሰብ ተወካዮች መካከል አቶ ካሳሁን ከሊፋ፣ አቶ ኪዳኔ አለማየሁ እና አቶ በቀሌ ኡሮ በዞኑ ኤሌክትሪክ አገልግሎት መቆራረጥ፣ የኢሰራ ባሌ ሆስፒታል ግንባታ በተያዘው ጊዜ አለመጀመር፣ የወልዳ ሃኔ-ዱርጊ-ዱራሜ መንገድ፤ የታርጫ-ወልዳ ሃኔ-ወራቦ፤ የዋካ-ኢሰራ መንገድ፤ የአንገላ-ዳሻ መንገድ መሠረተ ልማት ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙም ጠይቀዋል።

በመድረኩ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ምክር ቤት አፈ-ጉባኤ አቶ ወንድሙ ኩርታ፣ በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ተክሌ በዛብህ፣ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር እና የግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ማስረሻ በላቸውን ጨምሮ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ የዞን፤ የየወረዳዎቹ ተወካዮች፣ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የህብረተሰቡ ተወካዮች ተገኝተዋል።

ዘጋቢ፡ አዲስዓለም ታዬ – ከዋካ ጣቢያችን