ሲዳማ ቡና የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ አነሳ
በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን የሆነው ሲዳማ ቡና በዛሬው ዕለት በበርካታ ደጋፊዎቹ ፊት የሊጉን ዋንጫ ከፍ አድርጎ አንስቷል።
የ2018 የውድድር ዘመን ሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ የመጨረሻ ጨዋታ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ስታዲየም በሻምፒዮኑ ሲዳማ ቡና እና በኢትዮ ኤሌክትሪክ መካከል ተካሂዷል።
በበርካታ ደጋፊዎች እና የክብር እንግዶች ታጅቦ የተካሄደው የሁለቱ ክለቦች ጨዋታ በኢትዮ ኤሌክትሪክ 1ለ0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ውጤቱን ተከትሎ ሲዳማ ቡና 68 ነጥቦችን ይዞ ሊጉን በቀዳሚነት ሲያጠናቅቅ የውድድር ዓመቱን በድል የቋጨው ኢትዮ ኤሌክትሪክ 5ኛ ደረጃን በመያዝ የውድድር ዓመቱን አጠናቋል።
ሻምፒየኑ ሲዳማ ቡና በዘንድሮው የውድድር ዓመት በፕሪሚዬር ሊጉ ካከናወናቸው 38 ጨዋታዎች መካከል 19ኙን በድል የተወጣ ሲሆን በ11 ጨዋታዎች አቻ ተለያይቶ 8 ጨዋታዎችን ደግሞ በሽንፈት አጠናቋል።
አሊቶዎቹ በነዚህ ጨዋታዎች 43 ጎሎችን በተጋጣሚያቸው መረብ ላይ ሲያሳርፉ በአንፃሩ 23 ጎሎች ተቆጥሮባቸዋል።
ሲዳማ ቡና ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ የኢትዮጵያ ፕሪሚር ሊግ እንደ አዲስ ከተጀመረ በኋላ ዋንጫውን ያሸነፈ 11ኛው ክለብም ሆኗል፡፡
በተጨማሪም ከሀዋሳ ከተማ፣ከጅማ አባጅፋር፣መቀሌ 70 እንደርታ እና ፋሲል ከነማ በመቀጠል የፕሪሚዬር ሊጉን ዋንጫ ያነሳ 5ኛው የክልል ክለብም ሆኗል።
በዚህ ዓመት ምድረገነት ሽረ፣መቀሌ 70 እንደርታ፣ድሬዳዋ ከተማ እና አርባምንጭ ከተማ ከፕሪሚየር ሊጉ ወደ ከፍተኛ ሊጉ የወረዱ ክለቦች ናቸው።
በአንፃሩ ጋሞ ጬንቻ እና ሀላባ ከተማ ከከፍተኛ ሊጉ ወደ ፕሪሚዬር ሊጉ በማደግ በሚቀጥለው የውድድር በታሪካቸው ለመጀመሪያ ጊዜ በዋናው የሊግ ዕርከን የሚጫወቱ ይሆናል።
ሲዳማ ቡና የፕሪሚዬር ሊጉ ሻምፒዮን መሆኑን ተከትሎ በቀጣይ ኢትዮጵያን ወክሎ በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ይካፈላል።
ፕሪሚዬር ሊጉን በስኬት ያጠናቀቀው ሲዳማ ቡና የፊታችን ሐሙስ በኢትዮጵያ ዋንጫ ፍፃሜ ከወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ጋር ይፋለማል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማንቸስተር ዩናይትድ ግብ ጠባቂ አስፈረመ
ማንቸስተር ዩናይትድ አንድሬ ሳንቶስን አስፈረመ
የ2018 የCBE የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ እና የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት በታች ፕሪሚየር ሊግ ውድድርን በማሸነፍ ሁለት ዋንጫ ላነሳው የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ክለብ ክልሉ ያዘጋጀውን የዕውቅናና የሽልማት ፕሮግራም ዛሬ ሰኞ ሐምሌ 06/2018 ከቀኑ 12፡00 ጀምሮ በሀዋሳ ሀይሌ ሪዞርት ይካሄዳል።