የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር የሚያበረክተው አስተዋጽኦ ከፍተኛ መሆኑ ተገለጸ

የአውስትራሊያ ዓለም አቀፍ የግብርና ምርምር ማዕከል በካፋ ዞን አዲዮ ወረዳ ቦቃ ቀበሌ ለዘጠኝ ወራት በስርዓተ-ምግብና የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት ላይ ለነፍሰ-ጡር እናቶች ተግባር ተኮር ስልጠና ሰጥቷል።

በኢትዮጵያ የማዕከሉ አስተባባሪ ሽግዳፍ መኩሪያው(ዶ/ር) በዚህ ወቅት እንደገለጹት፤ የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓትን መከተል ጤናማ ትውልድ እንዲፈጠር ፋይዳው የጎላ ነው።

በወረዳው ቦቃ ቀበሌ ለዘጠኝ ወራት የስርዓተ-ምግብና የተመጣጠነ ምግብ አዘገጃጀት ላይ ለነፍሰ-ጡር እናቶች ተግባር ተኮር ስልጠና ሲሰጥ መቆየቱን ተናግረዋል።

ነፍሰ-ጡር እናቶች የተመጣጠነ አመጋገብ ስርዓቱን በመከተል የራሳቸውንና የልጆቻቸውን ጤንነት ለመጠበቅ የስርዓተ-ምግብ መመሪያን ማወቅ እንደሚገባቸውም አሰገንዝበዋል::

ፕሮጀክቱ በማህበርሰብ አቀፍ የበግ እርባታ ስራዎች ላይ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል።

በአካባቢው የሚገኙ የተለያዩ የምግብ አይነቶችን አመጣጥኖ መጠቀም የአመጋገብ ሥርዓትን በማሻሻል የአካል ጤንነትን ከመጠበቅ ባለፈ የአዕምሮ እድገትን ለማጎልበት ወሳኝ መሆኑን አስረድተዋል።

ምግብ በሚዘጋጅበት ወቅት ንፅህናውን በጠበቀ መልኩ ሊሆን እንደሚገባ ያሳሰቡት ደግሞ በቦንጋ ግብርና ምርምር ማዕከል የምግብ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ተመራማሪ አቶ መስፍን ወልዴ ናቸው::

በወረዳው ጤና ጽህፈት ቤት የእናቶችና ህፃናት ስራ ሂደት አሰተባባሪ አቶ ተሾመ ጩማሮ፤ ፕሮጀክቱ የእናቶችን ክህሎት በማጎልበት በቤተሰብ የምግብ አሰጣጥ ላይ ያላቸውን ዕውቀትና ክህሎት በማሳደግ ውጤት እያሰገኘ ነው ብለዋል።

የተመጣጠነ ምግብ አዘጋጃጀትና የጤና አጠባበቅ ላይ የተዘጋጀውን ሰነድ ያቀረቡት የቦቃ ጤና ጣቢያ ስራ አስኪያጅ አቶ አገኘሁ አባተ፤ ነፍሰ-ጡር እናቶች በእርግዝና ወቅት መከተል በሚገባቸው መሰረታዊ ጉዳዮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት ሰጥተዋል።

በአካባቢው የሚገኙና ለምግብነት የሚያገለግሉ ነገሮችን በማመጣጠንና በማዘጋጀት ጤናማ የአመጋገብ ስርዓትን መከተል ይቻላል ያሉት አቶ አገኘሁ፤ የምግብ ደህንነትን የሚያረጋግጡ የንጽህና አጠባበቅ ተግባራትን ለመለየት የሚያስችሉ ተግባራትን አቅርበዋል።

ተሳታፊ እናቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በሰጡት አስተያየት የተግባር ተኮር ስልጠናው የተመጣጠነ የአመጋገብ ሥርዓትን እንዲከተሉ የሚያስችል መሆኑን ተናግረዋል።

ስልጠናው በሌሎችም የተመረጡ መንደሮች የሚቀጥል እንደሆነ ተገልጿል፡፡

ዘጋቢ፡ ብዙአየሁ ጫካ – ከቦንጋ ጣቢያችን

ፎቶ፡ በረከት ገብረኪዳን