“እየተከልን ያለነው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነታችንን ጭምር ነው” – የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 30/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) “እየተከልን ያለነው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነታችንን ጭምር ነው” ሲሉ የኢፌዲሪ ውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር) ገለጹ፡፡
የውሃና ኢነርጂ ሚኒስቴር ከተጠሪ ተቋማቱ ጋር በመተባበር በሲዳማ ክልል ሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ሸበዲኖ ወረዳ አንፈራራ ቀበሌ ያካሄደው የአረንጓዴ አሻራና የክረምት የበጎ ፈቃድ መርሃ ግብር ከአካባቢ ጥበቃ ባለፈ ማህበራዊ ተጠያቂነትንና የምግብ ዋስትናን ያጠናከረ ተግባር ሆኗል።
በመርሃ ግብሩ የተገኙት የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር ኢንጂነር ሀብታሙ ኢተፋ(ዶ/ር)፤ “እየተከልን ያለነው ችግኝ ብቻ ሳይሆን የምግብ ሉዓላዊነታችንን ጭምር ነው” በማለት የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር የአፈር መሸርሸርን በመቀነስ፣ የውሃ ምንጮችን በማጠናከርና የምግብ ዋስትናን በማረጋገጥ ለዘላቂ ልማት መሠረት እንደሚሆን ገልጸዋል።
ሚኒስትሩ አክለውም፤ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በየዓመቱ እየተጠናከረ በመምጣት የተቋማት ባህል መሆኑን ጠቅሰው፤ ይህ ልምድ የማህበረሰቡን ችግር በመቅረፍ ዘላቂ ለውጥ ለማምጣት ከፍተኛ ሚና እንዳለው አስረድተዋል።
በእለቱ መርሃ ግብር በቀበሌው የተለያዩ ጠቀሜታ ያላቸው ከ50 ሺህ በላይ ችግኞች መተከላቸውንና ለ7 አቅመ ደካማ ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤት ግንባታ ስራ ተጀምሯል፡፡
በተጨማሪም ለ500 ደጋፊ የሌላቸው ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የተደረገ ሲሆን የደም ልገሳ መርሃ ግብርም ተካሂዷል።
የሰሜናዊ ሲዳማ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ፃዲቁ በጢሶ በበኩላቸው፤ ሚኒስቴሩ በዞኑ የውሃ፣ የኢነርጂና ሌሎች ዘርፈ ብዙ የልማት ሥራዎችን በማከናወን ለአካባቢው እያበረከተ ላለው አስተዋጽኦ ምስጋናቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ወንድወሰን ሽመልስ

More Stories
መሳላ የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው – የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች
የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ከብሔሩ ዘመን መለወጫነት ባሻገር የሚያበረክተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ነው – የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የ”ያሆዴ” በዓልን ስናከብር ስለ ሀገራችን ልማትና ስለ ህዝባችን አብሮነት የበለጠ የምንተጋበት ወቅት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል