የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር ለሕብረተሰቡ ግንዛቤን ከመፍጠር ጀምሮ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ መሆናቸውን በከምባታ ዞን የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት አስታወቀ።
በሺንሽቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ያነጋገርናቸው የህብረተሰብ ክፍሎች በበኩላቸው፤ የወባ በሽታን ከጤና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሰረት እየተከላከሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በጤና ባለሙያዎች በተፈጠረላቸው ግንዛቤ መሠረት የአካባቢውንና የግል ንጽህና በመጠበቅና የአልጋ አጎበር በአግባቡ በመጠቀም የወባ በሽታ እየተከላከሉ መሆናቸውንም ተገልጋዮቹ ተናግረዋል።
የወባ ትንኝ የሚረባበትን ቦታ በመድፈንና የአካባቢውን ቆሻሻ በተገቢው በማቃጠል በወባ በሽታ ከመጠቃት መታደግ መቻላቸውን አስተያየት ሰጪዎቹ ጠቁመዋል።
በሺንሽቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ተመላላሽ ህክምና ክፍል አስተባባሪ ዶ/ር ብሩክ ወ/ሚካኤል፤ በአካባቢው በስፋት ከሚከሰቱ የበሽታ አይነቶች ብሎም ከተመላላሽ ታካሚዎች መካከል በርካታዎቹ በወባ በሽታ የሚያዙ እንደነበር አስታውሰው በአሁኑ ጊዜ በሽታውን ለመቆጣጠር የተሰሩ ስራዎች ተጨባጭ ለውጥ እያመጡ እንደሆነ ተናግረዋል።
የሺንሽቾ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ስራ አስኪያጅ አቶ ሙሉቀን ማርቆስ በበኩላቸው፤ የወባ በሽታ የሚከሰተው በወባ ትንኝ አማካኝነት እንደሆነ ጠቅሰው፤ በሆስፒታል ደረጃ የወባ በሽታን ለመከላከልና ለመቆጣጠር በየቀኑ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ እየተፈጠረ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
የአካባቢው አየር ንብረት ለወባ በሽታ የሚያጋልጥ በመሆኑ አስቀድሞ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎች ላይ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መቆየቱን ያነሱት አቶ ሙሉቀን፤ በወባ በሽታ ለተያዙ ታካሚዎች መድኃኒት በነጻ እንደሚሰጥም ጠቅሰዋል።
የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ጤና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አለማየሁ ላፌቦ፤ የወባ በሽታ የቅድመ መከላከል ስራው በተገቢ ካልተሰራ የሰውን ህይወት በማጥፋት ሀገርን ለበርካታ ችግር የሚያጋልጥ በመሆኑ የበሽታውን የስርጭት መጠን ለመግታት በርካታ ስራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በከተማው ለወባ ትንኝ መራቢያ ምክንያት የሚሆኑ ውሃ ያቆሩ ቦታዎችን በመድፈን ሰዎች አጎበርን በአግባቡ እንዲጠቀሙ ማድረግን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎች መሰራታቸውንም ኃላፊው ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ ደሳለኝ ታደሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በከምባታ ዞን ሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር የኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ስርአት (E-LMIS) ምዝገባ በይፋ መጀመሩን የከተማው ኢንተርፕራይዝና ሥራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት አስታወቀ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በሆሳዕና ከተማ ሰኔ 11 ቀን 2018 ዓ.ም በተከሰተው ድንገተኛ የእሳት አደጋ ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች ድጋፍ ተደረገ
ህብረተሰቡ የኤሌክትሪክ መስመሮችን ጨምሮ ለእሳት አደጋ መንስኤ የሚሆኑ የመጠቀሚያ ዕቃዎችን በጥንቃቄ በመጠቀም በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የሚደርሰውን ጉዳት መከላከል እንደሚገባ ተገለጸ