በከምባታ ዞን የሺንሽቾ ከተማ የመሠረተ ልማት ተግባራት በማጠናከር የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ
በከተማ አስተዳደሩ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍና የኮሪደር ልማት ስራዎች እየተሰሩ ስለመሆናቸውም ተመላክቷል።
መንግሥት ከተሞችን በማዘመን የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሰራ ይገኛል።
ለዚህም በሀገሪቱ የተለያዩ ከተሞች የኮሪደር ልማትን ጨምሮ የመሠረተ ልማት ስራዎች እየተሰሩ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው።
በከምባታ ዞን የሺንሽቾ ከተማ ነዋሪዎች በሀገሪቱ በአንዳንድ ከተሞች እየተሰራ የሚገኘው የኮሪደር ልማት ስራ ከከተማው መጀመሩ እንዳስደሰታቸው ገልጸው እየተሰራ የሚገኘው የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ የህዝቡ ፍላጎት እንደሆነ ተናግረዋል።
አሁን ላይ በከተማ አስተዳደሩ በጀት የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በቀጣይ በልማቱ መሳተፍ እንዲችሉ እንዳነሳሳቸውም ተናግረዋል።
የሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ መለሰ ገቡሬ ከተማውን ለኑሮ ምቹና ውብ በማድረግ የነዋሪውን የመሠረተ ልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በተለያዩ መስኮች እቅድ ተነድፎ እየተሰራ መሆኑን ገልጸዋል።
አሁን ላይ የተጀመረው የኮርደር ልማት ስራና የውስጥ ለውስጥ ጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ የዚሁ አካል እንደሆነም ከንቲባው አመልክተዋል።
በቀጣይ ያሉ አቅሞችን አሟጦ በመጠቀምና ህብረተሰቡን በማሳተፍ ውጤታማ የልማት ስራዎች እንደሚሰሩ ያብራሩት አቶ መለሰ በዚህም ነዋሪው በሚያስፈልገው ሁሉ የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ ከንቲባ ጥሪ አስተላልፈዋል።
በሺንሽቾ ከተማ አስተዳደር ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት ጽ/ቤት ምክትል ስራ አስኪያጅና የማስፈፀም ዘርፍ ሀላፊ አቶ ሀያልሰው ሀይለማሪያም፤ አሁን ላይ በከተማው የተጀመረው የኮሪደር ልማት ስራ በቀጣይ በከተማው ለሚከናወኑ የልማት ተግባራት አጋዥ በመሆኑ የነዋሪውን ፍላጎት ባማከለ መልኩ በጥራት እንደሚሰራ ተናግረዋል።
የኮሪደር ልማት ስራው በ 2 ሺህ 2 መቶ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈ የብስክሌትና የእግረኛ መንገድ ያለው፣ የመብራት ፖሎችን ጨምሮ የተለያዩ መዝናኛዎች ያሉት እንደሆነ የተናገሩት አቶ ሀያልሰው ሀይለማሪያም፤ ስራዎቹም በአጭር ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው ለአገልግሎት ክፍት እንደሚሆኑ አብራርተዋል።
በሌላ በኩል 7 ሺህ 9 መቶ ካሬ ሜትር የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራ እየተከናወነ መሆኑን የጠቁሙት ሀላፊው፤ በቀጣይ በሶስት ሳይቶች አዳዲስ የጌጠኛ ድንጋይ ንጣፍ ስራዎች እንደሚጀምሩ አስታውቀዋል።
ስራዎቹ በጥራትና በፍጥነት እንዲጠናቀቁ ልዩ ትኩረት ይደረጋልም ብለዋል ኃላፊው።
ዘጋቢ፡ ደሳለኝ ታደሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ86 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ መሆኑ ተገለፀ
የተቀናጀ የመሬት አያያዝ ፖሊሲ የቡና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ተገለፀ
የቀርከሃ ምርትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊስሩ እንደሚገባ በኣሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ጠየቁ