የተቀናጀ የመሬት አያያዝ ፖሊሲ የቡና ምርታማነትን እንደሚያሳድግ ተገለፀ
የተቀናጀ የመሬት አያያዝ ፖሊሲን መተግበር የቡና ነቀላና እደሳ ሥራዎችን በተሻለ እውቀትና ቴክኖሎጂ ለማከናወን እንደሚያስችል በጌዴኦ ዞን ኮቾሬ ወረዳ የተካሄደ የባለድርሻ አካላት ውይይት አመላክቷል።
በወረዳው የተቀናጀ የመሬት አጠቃቀምና አያያዝ እቅድን አጽድቆ ወደ ትግበራ ለማስገባት የተዘጋጀው የጋራ ምክክር፣ የመሬትን ሀብት በሳይንሳዊ መንገድ ለማስተዳደር የሚያስችሉ አሠራሮች ላይ አተኩሯል።
የኮቾሬ ወረዳ መሬት አስተዳደር ጽህፈት ቤት የገጠር መሬት አስተዳደርና አጠቃቀም ቡድን መሪ አቶ ተጌጠ እንቁስላሴ እንደገለጹት፤ በወረዳው የመሬት አጠቃቀም በብዛት በባህላዊ አሠራር የሚከናወን በመሆኑ ለመሬት መበጣጠስና ለአካባቢ ችግሮች እየዳረገ ነው።
የመሬት አጠቃቀም እቅድን በሳይንሳዊ መንገድ መተግበር ግን በአነስተኛ መሬት ላይ ከፍተኛ ምርት ለማግኘት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
የኮቾሬ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ማሮ በበኩላቸው፣ በፌዴራል መንግስት እና በፎሉር ፕሮጀክት ድጋፍ የተዘጋጀው እቅድ ለዘላቂ የመሬት አስተዳደርና ለምርታማነት መጨመር ጉልህ አስተዋፅኦ እንደሚኖረው ገልጸው ፕሮጀክቱ አሁን በአምስት ቀበሌያት የሚተገበር ቢሆንም ወደ ሌሎች 19 ቀበሌያት ለማስፋፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስታውቀዋል።
በውይይቱ የተሳተፉ የአንጨቢና እና የጃልዶ ቀበሌ የመሬት አስተዳደር ባለሙያዎች፤ የመሬት አጠቃቀም ፖሊሲው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ ያለውን ጠቀሜታ መገንዘባቸውን ገልጸው ለተግባራዊነቱ በቅንጅት እንደሚሠሩ አረጋግጠዋል።
ዘጋቢ፡ ውብሸት ካሳሁን – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን

More Stories
በከምባታ ዞን የሺንሽቾ ከተማ የመሠረተ ልማት ተግባራት በማጠናከር የነዋሪዎችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የከተማው አስተዳደር አስታወቀ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከ86 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ተማሪዎች የ8ኛ ክፍል ክልላዊ ፈተና እየተሰጠ መሆኑ ተገለፀ
የቀርከሃ ምርትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊስሩ እንደሚገባ በኣሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ጠየቁ