የቀርከሃ ምርትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊስሩ እንደሚገባ በኣሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ጠየቁ‎

የቀርከሃ ምርትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊስሩ እንደሚገባ በኣሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳ የሚገኙ አርሶ አደሮች ጠየቁ

‎የቀርከሃ ምርት እጅግ በጣም ፈጣን እድገት ያለው ጠንካራ የተፈጥሮ የሣር ዝርያ ነው።

‎ይህም ምርት ለህንፃ ግንባታ፣ ለቤት ውስጥ የዕደ ጥበብ ውጤቶች፣ ለምግብነት፣ ለወረቀት ምርት እንዲሁም ለልብስና ጫማ ማምረቻነት በስፋት ያገለግላል።

‎በተጨማሪም አካባቢን ከብክለት ለመጠበቅና በከባቢ አየር ውስጥ የሚገኙ ካርቦኖችን በፍጥነት በመሳብ የአየር ንብረት ለውጥን ከመከላከል ጀምሮ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው።

‎በኣሪ ዞን ዎባ ኣሪ ወረዳም ይህ ምርት በስፋት ከሚመረትባቸው አከባቢዎች አንዱ ነው።

‎ይሁን እንጅ በወረዳው የሚገኙ አርሶ አደሮችም በየማሳዎቻቸው ይህንን ምርት አብዛኛውን ጊዜ በማምረት ለጎጆ ቤት መስሪያ፣ ለአጥር እና ለሌሎች አገልግሎቶች ከመጠቀም ባለፈ በዘርፉ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን በሚያሳድግ መልኩ በገቢ ምንጭነት እየተጠቀሙ አለመሆኑን ይናገራሉ።

‎በመሆኑም ለዘርፉ ውጤታማነት መንግስትና ሌሎች የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትኩረት ሰጥተው ሊስሩ ይገባል ሲሉ ጠይቀዋል።

‎የኣሪ ዞን የዎባ ኣሪ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፈጠነ አየነው በበኩላቸው እንደገለፁት፤ በወረዳው የቀርከሃ ምርት በአብዛኛው አርሶ አደር ማሳ በስፋት እንደሚመረትና ይህንን ምርት ማህበረሰቡ በአግባቡ እንዲጠቀሙ የማስገንዘብ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

‎በዚህም በወረዳ ደረጃ አጠቃላይ የቀርከሃ ምርት ሽፋን ከ20 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት የደረሰ ሲሆን፤ ምርቱ በአስተማማኝ ሁኔታ ለወረዳውም ሆነ ለማህበረሰቡ በገቢ ምንጭነት እንዲያገለግል በቀጣይ በተደራጀ መንገድ እንደሚሰራ ኃላፊው አቶ ፈጠነ አመላክተዋል።

‎ዘጋቢ: ፍቃዱ ግዲ – ከጂንካ ጣቢያችን