አርጅቶ ያልደከመው ሊዮኔል ሜሲ
በዓለም እግር ኳስ መድረክ ላይ ኮከቦች ቢበራከቱም፣ የሊዮኔል ሜሲን ያህል ብርሃን የፈነጠቀ ግን አልነበረም።
በካንሳስ ሲቲ በተካሄደው የአርጀንቲናና የአልጄሪያ ጨዋታ፣ የ38 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ በዓለም ዋንጫ ታሪክ የራሱን ስም በወርቅ ቀለም አስፍሯል።
አርጀንቲና አልጄሪያን 3-0 በሆነ ውጤት ስታሸንፍ፣ የሁሉም ትኩረት የነበረው በሜሲ ላይ ነበር።
በጨዋታው ሦስት ጎሎችን ያስቆጠረው ሊዮኔል ሜሲ ከጨዋታው መጠናቀቅ በኋላ በዓለም ዋንጫው አስደናቂ ታሪካዊ እውነታዎችን አስመዝግቧል።
ሜሲ በስድስት የተለያዩ የዓለም ዋንጫዎች ላይ የተሳተፈ የመጀመሪያው ተጫዋች በመሆን ክብረ ወሰኑን ሰብሯል። ይህም ከባላንጣው ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአንድ ቀን እንዲቀድም አድርጎታል።
ሜሲ ባስቆጠራቸው ሦስት ግቦች፣ በዓለም ዋንጫ ታሪክ ያስቆጠራቸውን ግቦች ብዛት 16 አድርሷል። ይህ ውጤት ከጀርመኑ ሚሮስላቭ ክሎዝ ጋር በዓለም ዋንጫ ታሪክ ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት ክብረወሰንን እንዲስተካከል አድርጎታል።
አልጄሪያ ላይ ያስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች ለሜሲ የመጀመሪያው የዓለም ዋንጫ ሀት-ትሪክ ሆኗል።
በምሽቱ ጨዋታ ከመጀመሪያው ደቂቃ ጀምሮ ሜሲ በከፍተኛ መነሳሳት ላይ ሆኖ ተስተውሏል።
በ18ኛው ደቂቃ ላይ ከ25 ሜትር ርቀት በመምታት ያስቆጠራት ግብ የስታዲየሙን ደጋፊዎች በጩኸት ያናወጠች ነበር። የቀድሞው የእግር ኳስ ተጫዋች ሊዮን ኦስማን በሜሲ ብቃት ተደንቆ፣ “ሜሲ ጎሉን ካስቆጠረ በኋላ ያሳየው ደስታ አገላለፅ ገና የመጀመሪያ ግቡን እንዳስቆጠረ ተጫዋች ነው፤ እድሜው እየጨመረ ቢመጣም ብቃቱ ግን እንደ ወጣት ይንቀሳቀሳል” ሲል ተናግሯል።
ሜሲ ሁለተኛ ግቡን በ60ኛው ደቂቃ፣ ሦስተኛውን ደግሞ በ76ኛው ደቂቃ በማስቆጠር ድሉን አሳምሮታል።
የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ከሜዳ ሲወጣ፣ በስታዲየም የነበሩት ደጋፊዎች በጭብጨባና በሜሲ ስም ጥሪ ሜዳውን ሲያናውጡት ተስተውሏል።
ሊዮኔል ሜሲ ከጨዋታው በኋላ በሰጠው አስተያየት፣ ለቤተሰቡ፣ ለቡድን አጋሮቹ እና ለደጋፊዎቹ ያለውን ምስጋና ገልጿል።
“ሁሉንም ነገር እንደ ድጋፍ ነው የምቆጥረው። በተጫዋችነቴ ሆነ በግል ህይወቴ ካሰብኩት በላይ ስኬታማ ሆኛለሁ፤ አሁንም ለሀገሬ መጫወቴ ትልቅ ደስታ ነው” በማለት በስሜት ተናግሯል።
የአሰልጣኝ ሊዮኔል ስካሎኒ አስተያየትም የሜሲን በቡድኑ ውስጥ ያለውን ተጽእኖ የሚያሳይ ነበር።
“ሜሲን ለመግለጽ ቃላት ያንሱኛል። ላለፉት 20 ዓመታት እኛን እንዲህ አይነት ነገሮችን በማሳየት አስደምሞናል፤ የሚያየው ሁሉ በእሱ ይነሳሳል” ሲሉ ተናግረዋል።
የ38 ዓመቱ ሊዮኔል ሜሲ እድሜ ለስኬቱ እንቅፋት እንዳልሆነ በድጋሚ አረጋግጧል።
አርጀንቲና የዓለም ዋንጫውን ለማሸነፍ በሜሲ ላይ ያላት ተስፋ አሁንም ከፍ ያለ ሲሆን፣ በካንሳስ ሲቲ የታየው የሜሲ ብቃት ለሌሎች ተፎካካሪዎች ትልቅ መልእክት ያስተላለፈ ምሽት ነበር።
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ከቦንዲ ጎዳናዎች እስከ ፈረንሳይ የታሪክ አናት
ከ4 ሺህ 337 ቀናት በኋላ በአሜሪካ ምድር የሚጫወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ፈረንሳይ እና ሴኔጋል ዳግም በአንድ መድረክ!