ከቦንዲ ጎዳናዎች እስከ ፈረንሳይ የታሪክ አናት
ፈረንሳይ በታሪኳ ከዚህ ቀደም እንደ ዙኔዲን ዚዳን፣ ሚሼል ፕላቲኒ እና ቲየሪ ሄንሪ ያሉ የዓለም እግር ኳስን መቆጣጠር የቻሉ ክዋክብቶችን አፍርታለች።
ይሁን እንጂ ዛሬ የፈረንሳይ እግር ኳስ ታሪክ አዲስ ምዕራፍ ተከፍቷል።
በ27 ዓመቱ ኪሊያን ምባፔ ትናንት ምሽት በሴኔጋል ላይ ባስቆጠራቸው ግቦች የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ በመሆን የኦሊቪዬ ዢሩን ክብረ ወሰን መስበር ችሏል።
በአጠቃላይ 58 ግቦችን በ99 ጨዋታዎች ያስቆጠረው ምባፔ፣ የራሱን ታሪክ እየጻፈ ብቻ ሳይሆን፣ ወደፊትም የማይደፈር የክብረ ወሰን ተራራ እየገነባ ነው።
የምባፔ ስኬት በአጋጣሚ የመጣ አይደለም።
ቤተሰቡ ገና ከልጅነቱ ጀምሮ ለዚህ ቀን ያበቃው “ፕሮጀክት ምባፔ” የተሰኘ ስልታዊ እቅድ ነበራቸው።
ገና በሦስት ዓመቱ የፈረንሳይን ብሔራዊ መዝሙር መማሩ፣ ለእግር ኳስ የነበረው ከፍተኛ ፍቅር እና ራሱን እንደ ብሔራዊ ተጫዋች የመመልከቱ ሚስጥር ማሳያ ተደርጎ ይወሰዳል።
የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ዲዲዬ ዴሻምፕ በ2023 የቡድኑ አምበል አድርገውት ነበር።
እንደ እግርኳስ ተንታኙ ጁሊያን ሎረንስ ገለጻ፣ ምባፔ ከግብ አስቆጣሪነቱ ባሻገር በሜዳ ውስጥ ያለው ተጽዕኖ እና የቡድን መሪነቱ ከዚዳን እና ፕላቲኒ ጋር የሚያስተካክለው ብቃት አለው።
ምባፔ በዓለም ዋንጫ መድረክ ላይ እያሳየ ያለው ብቃት አስደናቂ ነው።
በዓለም ዋንጫ ጨዋታዎች 14 ግቦችን ያስቆጠረው ምባፔ፣ የጀርመኑን ሚሮስላቭ ክሎዜን እና የአርጀንቲናዊው ኮከብ ሊዮኔል ሜሲ (16 ግቦች) ክብረ ወሰን ለመስበር ሁለት ግቦች ብቻ ቀርተውታል።
በ2022 የዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ያስቆጠራቸው ሦስት ጎሎች፣ እንደ ጄፍ ሁርስት በዓለም ዋንጫ ፍጻሜ ሃት-ትሪክ የሰራ ሁለተኛው ተጫዋች አስብሎታል።
በሞናኮ ታዳጊ ኮከብ ሆኖ የጀመረው ጉዞው፣ በፒኤስጂ በኩል አልፎ አሁን በሪያል ማድሪድ ማረፉ፣ ለዓመታት ሲጠበቅ የነበረው የህልሙ መገለጫ ነው።
የቀድሞው የቡድን አጋሩ ኦሊቪዬ ዢሩ ስለ እርሱ ሲናገር “እሱ በተፈጥሮው መሪ ሆኖ ነው የተወለደው። የሚሄድበትን መንገድ ጠንቅቆ ያውቃል፤ በቅርብ ጊዜ ውስጥ 100 ግቦችን ያስቆጥራል ብዬ አምናለሁ” ሲል ምስክርነቱን ሰጥቷል።
የእግር ኳስ ተንታኙ ጁሊያን ሎረንስ በበኩሉ፡ “በእግርኳስ ተጫዋችነት ዘመኑ ማገባደጃ ላይ ምባፔ የፈረንሳይ የምንግዜም ምርጥ ተጫዋች እንደሚሆን ጥርጥር የለኝም። የእርሱ የዋንጫ መደርደሪያ ከዚዳን እና ፕላቲኒ ይበልጣል” በማለት ትንበያውን አስቀምጧል።
ምንም እንኳን በአገር አቀፍ ደረጃ አናት ላይ ቢሆንም፣ ምባፔ አሁንም የሚናፍቃቸው ሁለት ትላልቅ ሽልማቶች አሉት፡ የባሎንዶር ሽልማት እና የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን ማሸነፍ።
በአሥር ዓመቱ የናይኪ ስፖንሰርሺፕ ያገኘው፣ በ14 ዓመቱ ሞናኮን የተቀላቀለ እና በ19 ዓመቱ የዓለም ዋንጫን ያነሳው ምባፔ፣ የዘመናችን ትልቁ የእግር ኳስ ውጤት ነው።
የልጅነት ህልሙ “ኤል ማኢስትሮ” (መምህር) መሆን ነበር፤ ዛሬ ደግሞ ያ ህልም እውን ሆኖ ዓለምን በብቃቱ እያስተማረ ይገኛል።
ታዲያ የዓለም እግር ኳስ አዲሱ ንጉሥ ምባፔ፣ በቀጣዮቹ የዓለም ዋንጫዎች የክሎዜን እና የሜሲን ክብረ ወሰን ሰብሮ የዓለም የእግር ኳስ ታሪክን በራሱ ስም ይፅፍ ይሆን?
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አርጅቶ ያልደከመው ሊዮኔል ሜሲ
የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በሥርዓተ ፆታ ዙሪያ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሃመድ ናስር ገለፁ
ከ4 ሺህ 337 ቀናት በኋላ በአሜሪካ ምድር የሚጫወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ