የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በሥርዓተ ፆታ ዙሪያ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሃመድ ናስር ገለፁ

የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በሚደረገው ጥረት በሥርዓተ ፆታ ዙሪያ የሚስተዋሉ የአመለካከት ችግሮችን መቅረፍ እንደሚገባ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሃመድ ናስር ገለፁ

ኃላፊዋ ይህን የገለፁት የክልሉ አመራር አካዳሚ ከክልሉ ሴቶችና ህፃናት ቢሮ ጋር በመተባበር “በሴክተር ማኔጅመንት ውስጥ የሴቶች ተሳትፎና ሥርዓተ ፆታን ማካተት ትግበራ ሂደት” በሚል የተጠና ጥናት ውጤት ማረጋገጫ መድረክ በተካሄደበት ወቅት ነው።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ህፃናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ ወ/ሮ ዘቢባ መሃመድ ናስር እንዳሉት፤ የጥናቱ ዓላማ የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ከማሳደግ በተጓዳኝ ያላቸውን እምቅ አቅም ለመጠቀምና ሃገርን ለማሳደግ ነው።

እካዳሚው በሴቶች ዙሪያ ያጠናው ጥናት የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነትን አጉልቶ የሚያሳይ መሆኑንም አስታውቀዋል።

መንግስት በየተቋማቱ የሴቶችን የስራ ጫና ለመቀነስና ሃላፊነታቸውን በተገቢው እንዲወጡ ለማስቻል የህፃናት ማቆያ እንዲገነባ እንደ ሃገር አቅጣጫ ቢቀመጥም እየተስተዋለ ያለውን ክፍተት በዘላቂነት መቅረፍ ይገባል ነው ያሉት።

ለዚህም የሴቶችና ህፃናት ተቋማት ከሚያደርጉት እንቅስቃሴ ባሻገር የፐብሊክ ተቋማት እገዛ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል።

አክለውም የሴቶች ተሳትፎና ተጠቃሚነትን በዘላቂነት ለማሳደግ በሚደረገው እንቅስቃሴ የሥርዓተ ፆታ አመለካከትን መቀየር ያሻል ሲሉም ተደምጠዋል ወ/ሮ ዘቢባ።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ዋና ዳይሬክተር አቶ ተስፋዬ ብላቱ በበኩላቸው፤ አካዳሚው በተለያዩ ዘርፎች ስልጠና የመስጠትና ጥናትና ምርምር የማካሄድ ተቋማዊ ተልዕኮውን ለመወጣት እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

በዚህም የሴቶችን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት በሴክተር ደረጃ ምን ያህል ነው በሚል የተዘጋጀው ጥናት የተመረጠበት ዋናው ምክንያት እንደ ዓለም በተጠኑ ጥናቶች የሴቶች ተሳትፎ በበዛባቸው ተቋማት የተሻለ ውጤት መመዝገቡን መነሻ በማድረግ ነው ብለዋል።

ተቋማት ከማጠናከር አኳያ ሴቶች ስኬታማ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ፤ ዘላቂ ልማትና ሰላምን ከማረጋገጥ አኳያም የማይተካ ሚና እንዳላቸው አስረድተዋል።

ይሁን እንጂ ተሳትፏቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ከማረጋገጥ ጋር ተያይዞ የሚታዩ ክፍተቶች ሰፊ መሆናቸውን አንስተው በቀጣይ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አፅንኦት ሰጥተዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል አመራር አካዳሚ ምክትልና የጥናትና ምርምር ዘርፍ ሀላፊ አቶ ከይረዲን ራህመቶ፤ ጥናቱ የሴቶች ተሳትፎ በማኔጅመንትና በሴክተር ደረጃ ሥርዓተ ፆታን ማካተት አስመልክቶ የቀረበው የጥናት ውጤት ብዙ አዳዲስ ውጤቶችን አስገኝቷል ብለዋል።

ከዚህ ቀደም የሴቶች ውሳኔ ሰጭነት ከአመራር ጋር ብቻ ይታይ እንደነበረ አስታውሰው ጥናቱ መሰረት አድርጎ የተነሳው ግን ከማኔጅመንት አካላት ጀምሮ እንደሆነ ጠቁመዋል።

በዚህም በደጋፊ የስራ ሂደቶች ሴቶች የሚበዙበትና በአስፈፃሚ የስራ መደቦች ላይ ደግሞ ቁጥራቸው ዝቅተኛ መሆኑ በጥናቱ መገኘቱን ገልፀዋል።

ይህንን ችግር በመቅረፍ የሃገር ለውጥና ብልፅግናን ለማረጋገጥ ሴቶችን ማሳተፍ የአማራጭ ጉዳይ ሳይሆን የህልውና መሆኑን አቶ ከይረዲን አንስተዋል።

የስልጠናው ተሳታፊዎች በሠጡት አስተያየት ጥናቱ ገላጭና አስተማሪ መሆኑን ጠቁመው ስለሆነም በዘርፉ የሚስተዋለውን የአመለካከት ችግር ለማረም ርብርብ እንደሚጠይቅ ተናግረዋል።

ሴቶች ወደ ሀላፊነት እንዲመጡ ከሀላፊዎች ባሻገር ሴቶች ራሳቸው እችላለሁ የሚለውን መንፈስ በመላበስ መስራት እንደሚጠበቅባቸው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ፡ እቴነሽ ቲሬቦ – ከወልቂጤ ጣቢያችን