ከ4 ሺህ 337 ቀናት በኋላ በአሜሪካ ምድር የሚጫወተው ክርስቲያኖ ሮናልዶ
ፖርቹጋላዊው ኮከብ ክርስቲያኖ ሮናልዶ ከ4,337 ቀናት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ በአሜሪካ ምድር ዳግም ለጨዋታ ይቀርባል።
የ41 ዓመቱ አምበል በ2026ቱ የፊፋ ዓለም ዋንጫ ፖርቹጋል ከዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ጋር በምድብ 11 በነገው ዕለት በሚያደርጉት የምድብ የመክፈቻ ጨዋታ ላይ በሂዩስተን፣ ቴክሳስ ይሰለፋል ተብሎ ይጠበቃል።
የአምስት ጊዜ የባሎንዲኦር አሸናፊው ክርስቲያኖ ተሰልፎ የሚጫወት ከሆነ በአሜሪካ ምድር ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚጫወት ይሆናል።
ክርስቲያኖ ሮናልዶ በአሜሪካ የመጨረሻው የጨዋታ ተሳትፎው የነበረው እ.ኤ.አ በ2014 ሲሆን፣ በዚያን ጊዜ ሪያል ማድሪድን ወክሎ ማንቸስተር ዩናይትድን የገጠመበት የዓለም አቀፍ ሻምፒዮንስ ዋንጫ ጨዋታ ላይ ነበር።
ከዚያ ወዲህ በግል ጉብኝቶች አሜሪካን ቢረግጥም፣ ምንም ዓይነት የፉክክር ጨዋታ አላደረገም ነበር።
ምንም እንኳን ባለፈው ህዳር ወር ላይ ፖርቹጋል በዓለም ዋንጫ ማጣሪያ ከሪፐብሊክ አየርላንድ ጋር በተደረገ ጨዋታ ቀይ ካርድ ተመልክቶ የነበረ ቢሆንም፣ የፊፋ ዲሲፕሊን ኮሚቴ ባሳለፈው ውሳኔ ቅጣቱ በመቀነሱ በነገው የመክፈቻ ጨዋታ ላይ የመሰለፍ እድል አግኝቷል።
ይህም በዓለም ዋንጫው የመክፈቻ ጨዋታ ላይ እንዲሰለፍ እድል ሰጥቶታል።
ሮናልዶ አሁንም የቡድኑ የልብ ትርታ በመሆን በአሰልጣኝ ሮቤርቶ ማርቲኔዝ ስር ከፍተኛ ግምት የሚሰጠው ተጫዋች ነው።
ምንም እንኳን የእድሜው ጉዳይ እና የቅርብ ጊዜ አቋሙ ጥያቄ ቢነሳበትም፣ በሜዳ ላይ ያለው መገኘት እና ልምድ ለፖርቹጋል ስኬት ወሳኝ እንደሆነ ይታመናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
“ማንቸስተር ሲቲ በዚህ አጨዋወት ሊጉን ማሸነፍ አይችልም”ፖል ሜርሰን
ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስርና አንድነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ
ከ1500 በላይ ኤሊት አትሌቶች የሚሳተፉበት 6ኛው ዙር የኬሮድ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወልቂጤ ከተማ ተጀመረ