ፈረንሳይ እና ሴኔጋል ዳግም በአንድ መድረክ!
የዓለም እግር ኳስ አድናቂዎች በጉጉት የሚጠባበቁት የፈረንሳይ እና የሴኔጋል ፍልሚያ፣ የ2002ቱን አስደናቂ ታሪክ የሚያስታውስ ነው።
በኒው ዮርክ ሜትላይፍ ስታዲየም ዛሬ ምሽት 4 ሰዓት ላይ የሚደረገው ይህ የምድብ ማጣሪያ ጨዋታ፣ በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
እ.ኤ.አ በ2002 የዓለም ዋንጫ መክፈቻ ጨዋታ፣ ፈረንሳይ የዓለም ሻምፒዮንነቷን ለማስጠበቅ ወደ ሜዳ ገብታ ነበር።
ነገር ግን በወቅቱ በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫው ተሳታፊ የነበረችው ሴኔጋል፣ በፓፓ ቡባ ዲዮፕ ብቸኛ ጎል ዓለምን ያስደነቀ ድል አስመዘገበች።
ይህ ውጤት የሴኔጋልን የእግር ኳስ ጉዞ የለወጠ ሲሆን፣ ፈረንሳይን ደግሞ ከውድድሩ በጊዜ እንዲሰናበቱ ያደረገ መራራ ሽንፈት ነበር።
የፈረንሳይ ብሔራዊ ቡድን ከ24 ዓመታት በፊት የደረሰውን ጠባሳ ለመሻር እና ጠንካራ መነሻ ለማድረግ በከፍተኛ ተነሳሽነት ዛሬ ወደ ሜዳ ይገባል።
ክሊያን ምባፔ በዓለም ላይ ካሉ ፈጣን እና አደገኛ አጥቂዎች አንዱ በመሆኑ፣ የሴኔጋልን የተከላካይ ክፍል ክፉኛ እንደሚፈታተን ይጠበቃል።
ሴኔጋል በበኩሏ በሳዲዮ ማኔ እየተመራች፣ ያንን በ2002 የነበረውን “የአንበሶች ጥንካሬ” ለመድገም ትጥራለች።
ማኔ ልምዱን ተጠቅሞ ቡድኑን በመምራት፣ ፈረንሳይን በድጋሚ ለመርታት ዝግጁ ነው።
የፈረንሳይ የፈጠራ ችሎታ ያላቸው አማካዮች ከሴኔጋል ጠንካራ እና የተደራጀ የመከላከል አቅም ጋር የሚኖራቸው ትግል የጨዋታውን ውጤት ሊወስን ይችላል።
ሁለቱም ቡድኖች ዘመናዊ እና ፈጣን የእግር ኳስ ጨዋታን የሚጫወቱ በመሆናቸው፣ በሜዳው መሃል የሚደረገው የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ለድል ቁልፍ ይሆናል።
በዚሁ ምድብ የሚገኙት ኢራቅ እና ኖርዌይ ሌሊት 7 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን ያደርጋሉ፡፡
በምድብ 10 የተደለደሉት አርጀንቲና አልጄሪያ ደግሞ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ ጨዋታቸውን የሚያደርጉ ይሆናል፡፡
ዘጋቢ ፡ ሙሉቀን ባሳ
ፈረንሳይ እና ሴኔጋል ዳግም በአንድ መድረክ!

More Stories
“ማንቸስተር ሲቲ በዚህ አጨዋወት ሊጉን ማሸነፍ አይችልም”ፖል ሜርሰን
ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስርና አንድነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ
ከ1500 በላይ ኤሊት አትሌቶች የሚሳተፉበት 6ኛው ዙር የኬሮድ የ15 ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በወልቂጤ ከተማ ተጀመረ