ከ”ህልም” ወደ “ቅዠት” የተለወጠው የሳንቾ የኦልድ ትራፎርድ ቆይታ
እ.ኤ.አ በ2021 ጃደን ሳንቾ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ሲያመራ ብዙዎች እግር ኳሳዊ የጥበብ ምንጭ አድርገውት ነበር።
ከቦሩሲያ ዶርትሙንድ በበርካታ ሚሊየን ፓውንድ የፈረመው ይህ ወጣት ኮከብ የዩናይትድ አጥቂ መስመርን ወደ ሌላ ከፍታ ያሸጋግራል ተብሎ ተስፋ ተጥሎበት ነበር።
ሆኖም የ5 ዓመታት ቆይታው በውጤት ማነስ፣ በዲሲፕሊን ችግሮች እና በሚሊየኖች የሚቆጠር የገንዘብ ብክነት የታጀበ “የውድቀት ታሪክ” ሆኖ ተጠናቀቀ።
የሳንቾ ዝውውር ለማንቸስተር ዩናይትድ ከገንዘብ አንጻር ሲታይ እጅግ ውድ የሆነ ስህተት ነበር፡፡
የዝውውር ክፍያ፡ £73 ሚሊየን፣ ሳምንታዊ ደመወዝ፡ 250,ሺህ ፓዉንድ፣ ጠቅላላ የተገመተ ወጪዉ፡ ወደ 138 ሚሊየን ፓዉንድ የሚጠጋ ነዉ።
ጃደን ሳንቾ ለዩናይትድ በ83 ጨዋታዎች ውስጥ ማስቆጠር የቻለው 12 ጎሎችን ብቻ ነው። ይህ ማለት ለእያንዳንዱ ጎል ክለቡ የከፈለው ዋጋ እጅግ ከፍተኛ ነበር።
ሳንቾ ወደ ክለቡ እንደመጣ የክርስቲያኖ ሮናልዶ መመለስ የቡድኑን አጨዋወት ቀይሮታል። በ ኦሌ ጉናር ሶልሻየር የተዘጋጀው እቅድ ለሳንቾ አጨዋወት የሚስማማ አልነበረም።
ከ ኤሪክ ቴን ሀግ ጋር የተፈጠረው የይፋዊ ግጭት የሳንቾን የዩናይትድ ቆይታ የመጨረሻ ምዕራፍ የከፈተ ነበር። በማህበራዊ ሚዲያ ላይ “የፍየል መስዋዕት” ነኝ በሚል የተናገረው ንግግር በአሰልጣኙ እና በተጫዋቹ መካከል ያለውን ድልድይ ሙሉ ለሙሉ አፍርሶታል።
በአንድ ወቅት ክለቡ ለሳንቾ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ለሦስት ወራት ከሜዳ እንዲርቅ እና እንዲያገግም እድል ሰጥቶት ነበር። ይህ በጎ እርምጃ ቢሆንም ወደ ሜዳ ሲመለስ የነበረው ብቃት የቀድሞውን ሳንቾ የሚያስታውስ አልነበረም።
ሳንቾ ወደ ዶርትሙንድ በተመለሰበት ወቅት፤ ወደ ቼልሲ እና አስቶንቪላ በተላከበት የውሰት ጊዜያት ሁሉ አውሮፓዊ ዋንጫዎችን (የዩኤፋ ኮንፍረንስ ሊግ እና ዩሮፓ ሊግ) ማሸነፉ ለዩናይተድ ደጋፊዎች ሌላኛው ቁስል ነበር።
በክለቡ ውስጥ መጫወት ያቃተው ኮከብ በሌሎች ክለቦች ውጤታማ መሆኑ ማንቸስተር ዩናይትድ ለተጫዋቾች የተመቻቸ አካባቢ የመፍጠር አቅሙ ጥያቄ ውስጥ እንዲገባ አድርጓል።
የሳንቾ ዝውውር የ”ሰር አሌክስ ፈርጉሰን” ዘመን ካበቃ ወዲህ ማንቸስተር ዩናይትድ ከፈጸማቸው እጅግ ውድ እና አስደንጋጭ የዝውውር ስህተቶች መካከል እንደ ዋና ምሳሌ የሚጠቀስ ሆኖ ይኖራል። ተስፋ የተጣለበት ኮከብ በክለቡ ታሪክ ውስጥ እንደ “የጠፋ እድል” ታሪክ ይዘከራል።
የሳንቾ ጉዳይ ለዘመናዊ እግር ኳስ ትልቅ ትምህርት ነው። አንድ ተጫዋች በሊግ (እንደ ቡንደስሊጋ) ጥሩ በመጫወቱ ብቻ በሌላ ሊግ (እንደ ፕሪሚዬር ሊግ) ስኬታማ ይሆናል ማለት አይደለም።
የክለቦች የዝውውር ፖሊሲ፣ የአሰልጣኞች ፍልስፍና እና የተጫዋቾች የስነ-ልቦና ዝግጁነት አንድን ተጫዋች ለስኬት ለማብቃት የጋራ ጥረት እንደሚጠይቁ ይህ ታሪክ በተግባር አሳይቷል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
ከ”ህልም” ወደ “ቅዠት” የተለወጠው የሳንቾ የኦልድ ትራፎርድ ቆይታ

More Stories
ፈረንሳይ እና ሴኔጋል ዳግም በአንድ መድረክ!
ሪያል ማድሪድ ማርክ ኩኩሬላን አስፈረመ
ኬፕ ቨርዴ በታላቁ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ