የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በመመለስ በኩል ከመንግስት ጥረት ባለፈ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና የጎላ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ተናገሩ

የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በመመለስ በኩል ከመንግስት ጥረት ባለፈ መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና የጎላ መሆኑን የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ ተናገሩ

ባለፉት አምስት አመታት ከ1 ቢሊየን ብር በላይ ወጪ የክልሉን የተፈጥሮ ሀብት በማሳደግ እና የመሬት ባለቤትነትን በማረጋገጥ በኩል ካልም የተባለ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ኃላፊነቱን መወጣቱ ተጠቁሟል።

በክልሉ ከሚንቀሳቀሱ መንግስታዊ ካልሆኑት ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው ካልም ፕሮጀክት የአመቱን እቅድ አፈጻጸም የባለድርሻ አካላት በተገኙበት ገምግሟል።

በዚሁ በእቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ የተገኙት የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተመስገን ከበደ እንደተናገሩት፤ በመንግስት ከሚከናወኑ የልማት ተግባራት ባለፈ የህዝቡን የልማት ተጠቃሚነት በማረጋገጥ በኩል መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች ሚና ከፍተኛ ነው።

ከእነዚህም መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ውስጥ አንዱ የሆነው የካልም ፕሮግራም በክልሉ ባለፉት አምስት አመታት በተለይም የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በክልሉ ስድስት ዞኖች በሚገኙ አርባ ወረዳዎች በተፋሰስ ልማት፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግብአት አቅርቦት ተግባራት እና በኑሮ ማሻሻያ፣ በመሰረት ልማት ስራዎች በርካታ ተግባራት ማከናወኑን ጠቁመዋል።

በዚህም የግብርናውን ስራ በማገዝ በኩል ፕሮጀክቱ ሚናውን ተወጥቷል ብለዋል።

በ2018 በጀት አመትም ከ320 ሚሊየን ብር በላይ በጀት መድቦ እየሰራ ሲሆን በተለይም በበጀት አመቱ የመረጃ አያያዝ ችግር፣ ወቅታዊ የኦዲት ስርአት አለማድረግ፣ የተላከውን ገንዘብ በወቅቱ ወደስራ አለመለወጥ ተግዳሮቶች ሲሆኑ ይህም መታረም እንዳለበት አቶ ተመስገን ተናግረዋል።

የደቡብ ምእራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ፋይናንስ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ሚሊዮን አለሙ በበኩላቸው፤ ካልም ፕሮግራም በክልሉ እያከናወነ ያለውን ጠንካራ ጎኖችን ለማስቀጠል እና በድክመት የሚታዩትን ለማረም ከባለድርሻ አካላት ጋራ ውይይት ማድረግ አስፈልጓል ብለዋል።

ውይይቱ የበጀት አመቱ ማጠቃለያ እንደመሆኑ መጠን በቀሪ ቀናት ቀሪ ተግባራትን ለማከናወን ያስችላል ብለዋል።

በውይይቱ ከፌደራል፣ ከክልሉ ስድስት ዞኖች የተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ተሳታፊ ሆነዋል።

ዘጋቢ: አብዮት በቀለ – ከሚዛን ጣቢያችን