ኬፕ ቨርዴ በታላቁ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ
በሰሜን አሜሪካ አስተናጋጅነት እየተካሄደ የሚገኘው የ2026 የዓለም ዋንጫ በታላላቅ ጨዋታዎች ቀጥሎ ይገኛል።
የዛሬው ምሽት መርሃ ግብር በተለይ ለእግርኳስ ቤተሰቦች ትልቅ ትኩረትን የሳበ ነው።
የዛሬው ምሽት ዋና መነጋገሪያ በምድብ 8 የሚደረገው የኬፕ ቨርዴ እና የስፔን ፍልሚያ ነው።
አፍሪካዊቷ ኬፕ ቨርዴ ለመጀመሪያ ጊዜ በዓለም ዋንጫ ታሪኳ መድረኩ ላይ መገኘቷ ለሀገሪቱ ስፖርት ትልቅ ምዕራፍ ነው።
ስፔን ብሔራዊ ቡድን ላይ ትልቅ ተስፋ የተጣለ ሲሆን፣ የስታቲስቲክስ ተቋሙ ኦፕታ ስፔንን የዘንድሮው ዋንጫ ዋና የዋንጫ ግምት ተቀዳሚ ተወዳዳሪ አድርጎ አስቀምጧታል።
በዛሬው ጨዋታ ስፔን በወረቀት ላይ የተሻለ ግምት ቢኖራትም፣ የኬፕ ቨርዴ ቡድን በአፍሪካ ማጣሪያዎች ያሳየው የአቋም ጥንካሬ እና ለመጀመሪያ ጊዜ የመሳተፍ መነቃቃት ተጋጣሚዋን ሊያስደነግጥ ይችላል።
በተለይም በታላላቅ መድረኮች የመጀመሪያ ጨዋታዎች ምንጊዜም ድንገተኛ ውጤት የሚያስተናግዱ በመሆናቸው፣ የዛሬው ምሽት የኬፕ ቨርዴ ህልም እውን የሚሆንበትን ውጤት እናያለን ወይ የሚለው በጉጉት የሚጠበቅ ነው።
ጨዋታዉ ምሽት 1:00 ሰዓት ላይ ይካሄዳል።
በምድቡ የኬፕ ቨርዴ እና ስፔንን ጨዋታ ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ከዩራጋይ ጋር የሚደርጉት ፍልሚያ፣ የሁለቱን ሀገራት የጥንካሬ ልክ የሚያሳይ ይሆናል።
ይህ ጨዋታ ሌሊት 7:00 ሰዓት የሚደረግ ይሆናል።
በምድብ ሰባትም የመጀመሪያ ዙር ጨዋታዎች ዛሬ ምሽት ሲካሄዱ ቤልጂየም ከ ግብፅ ጋር የሚገናኙበት ግጥሚያ በጉጉት ይጠበቃል።
አፍሪካዊቷ ግብፅ ከጠንካራዋ ቤልጂየም ጋር የምታደርገው ጨዋታ፣ የግብፅን የመከላከል እና የማጥቃት አቅም የሚፈትን ይሆናል።
ጨዋታው ምሽት 4 ሰዓት ላይ ነው የሚካሄደው።
በዚሁ ምድብ ኢራን ከኒውዚላንድ ጋር እንዲሁ ዛሬ ሌሊት ይጫወታሉ።
በምድቡ የነጥብ ፉክክር ለማድረግ የሚጫወቱት ሁለቱ ሀገራት፣ የራሳቸውን ታሪክ ለመፃፍ ወደ ሜዳ ይገባሉ።
ይህ ጨዋታ ደግሞ ሌሊት 10 ሰዓት ላይ የሚካሄድ ይሆናል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የአይቮሪኮስት የወደፊት ተስፋ
የዓለም ዋንጫውን የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው ጀርመን
ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን በእጅጉ ተቃረበ