የዓለም ዋንጫውን የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው ጀርመን
የጀርመን ብሔራዊ ቡድን በዓለም ዋንጫ ታሪክ ያስቆጠረውን የግብ ብዛት ወደ 239 በማድረስ የብራዚልን የረጅም ጊዜ ክብረ ወሰን በመስበር አዲስ ታሪክ ጽፏል።
ቀደም ሲል ብራዚል 238 ግቦችን በማስቆጠር የዓለም ዋንጫው የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪ ሀገር በመሆን ቀዳሚ ነበረች።
ሆኖም ጀርመን በኩራካኦ ላይ በሰባት ግቦች የታጀበ ድል በመቀዳጀት አህጉራዊ እና አለም አቀፋዊ የስፖርት መድረኮችን እያነጋገረ የሚገኝ ድንቅ ብቃቷን አሳይታለች።
ይህ ውጤት ጀርመን በውድድሩ ታሪክ ያላትን ልዩ የበላይነት በቁጥር የሚያሳይ ነው፡
የአራት ጊዜ የውድድር መድረኩ ባለክብሯ ጀርመን በአጠቃላይ 239 ግቦችን በማስቆጠር አንደኛ ደረጃን ይዛለች።
አውሮፓዊቷ ሀገር እነኚህን ጎሎች ለማስቆጠር 113 ጨዋታዎችን ማከናወን ግድ ብሏታል።
ጀርመን በውድድሩ ታሪክ በአማካይ በየጨዋታው ከሁለት ግብ በላይ ካስቆጠሩ ሦስት ሀገራት አንዷ ናት።
ይህንን አስደናቂ ታሪክ የያዙት ሀገራት የሚከተሉት ናቸው።
ሃንጋሪ 2.72 ግቦች በአማካይ፣ጀርመን 2.12 ግቦች በአማካይ እና ብራዚል 2.07 ግቦች በአማካይ አስቆጥረዋል።
በዓለም ዋንጫ ታሪክ 100 እና ከዚያ በላይ ግቦችን ማስቆጠር የቻሉት ሰባት ሀገራት ብቻ ሲሆኑ፤ ጀርመን ከዚህ ዝርዝር ውስጥ በግንባር ቀደምነት ትጠቀሳለች።
ይህ የጀርመን የግብ መጠን ክብረ ወሰን በቀላሉ የሚደፈር አይደለም።
ምንም እንኳን በዘመናዊው እግር ኳስ የቡድኖች የግብ ማግባት አቅም በየጊዜው ቢቀያየርም፤ ጀርመን በውድድሩ ላይ ያሳየችው የማጥቃት ጥራት የዘመናት ውጤት ነው።
ጀርመን ይህንን የግብ መጠን በዓለም ዋንጫው ላይ ማሳየቷ በተከላካይ መስመር ጥንካሬዋ ብቻ ሳይሆን በማጥቃት መስመሯም ስንት ጊዜ ታሪክ እንደሰራች የሚያስታውስ ነው።
ብራዚል ለረጅም ዓመታት ይዛው የነበረውን ይህንን ክብረ ወሰን መሻገሯ ለጀርመን እግር ኳስ አዲስ የክብር ምዕራፍ ነው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ
የዓለም ዋንጫውን የምንግዜም ከፍተኛ ግብ አስቆጣሪነት በቁጥጥሯ ስር ያዋለችው ጀርመን

More Stories
ኬፕ ቨርዴ በታላቁ መድረክ ለመጀመሪያ ጊዜ
የአይቮሪኮስት የወደፊት ተስፋ
ሲዳማ ቡና ኢትዮጵያ ቡናን በማሸነፍ የሊጉ ሻምፒዮን ለመሆን በእጅጉ ተቃረበ