በኢራን ጦርነት ማክተም ላይ የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት የአክሲዮን ገበያዎችን ሲያንረው ለነዳጅ ዋጋ መቀነስ ግን ምክንያት ሆኗል

በኢራን ጦርነት ማክተም ላይ የተደረሰው ጊዜያዊ ስምምነት የአክሲዮን ገበያዎችን ሲያንረው ለነዳጅ ዋጋ መቀነስ ግን ምክንያት ሆኗል

‎ሀዋሳ: ሰኔ 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ​በኢራን ጦርነት ማክተም እና የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት ዙሪያ ጊዜያዊ ስምምነት መደረሱ ይፋ መደረጉን ተከትሎ፥ ሰኞ ዕለት በኤዥያ የአክሲዮን ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል።

‎​በቶኪዮ እና በሴኡል የሚገኙ መመዘኛ ጠቋሚዎች (Benchmarks) ሰኞ ማለዳ ላይ መጀመሪያ አካባቢ ከ5% በላይ ጭማሪ አሳይተዋል። የነዳጅ ዋጋ ደግሞ በአንድ በርሜል ከ4 ዶላር በላይ ቀንሷል።

‎​ለኤስ ኤንድ ፒ 500 (S&P 500) እና ለዶው ጆንስ ኢንደስትሪያል ኤቨሬጅ (Dow Jones Industrial Average) የቀረቡ ትንበያዎች እንደቅደም ተከተላቸው የ1% እና የ0.9% ጭማሪ ማሳየታቸው፣ ለዎል ስትሪት (Wall Street) መጀመሪያ አካባቢ መልካም እመርታ ሊኖር እንደሚችል አመላካች ሆኗል።

‎​የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ የመጀመሪያ ደረጃ ስምምነቱን ያረጋገጡ ሲሆን፥ በኢራን የወደብ መግቢያዎች ላይ ተጥሎ የነበረው የአሜሪካ ባህር ኃይል እገዳ እንዲያበቃም ፈቅደዋል።

‎​ኢራንም ጉዳዩን ያረጋገጠች ቢሆንም ስምምነቱ ተግባራዊ መሆን የሚጀምረው ፓኪስታን በመጪው አርብ በስዊዘርላንድ ይካሄዳል ካለችው የፊርማ ሥነ-ሥርዓት በኋላ እንደሆነ ጠቁማለች።

‎የኢራንን የኑክሌር መርሃ-ግብር የመሳሰሉ ይበልጥ ሰፊ በሆኑ ጉዳዮች ላይ የሚደረጉ ድርድሮች በሚቀጥሉት 60 ቀናት ውስጥ ይቀጥላሉ ተብሎ ይጠበቃል።

‎​በሰኞ ማለዳ የንግድ ልውውጥ፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛ የሆነው የብሬንት ድፍድፍ ነዳጅ (Brent crude) ዋጋ በ3.61 ዶላር ቀንሶ በአንድ በርሜል 83.64 ዶላር ሆኗል። የአሜሪካ መመዘኛ ድፍድፍ ነዳጅ ደግሞ 4.27 ዶላር በማጣት በአንድ በርሜል 80.61 ዶላር ደርሷል።

‎​ሆኖም በጦርነቱ ሳቢያ በተፈጠሩ መስተጓጎሎች ምክንያት የነዳጅ ዋጋ በማሻቀቡና የነዳጅ እንዲሁም የሌሎች በርካታ ምርቶች ወጪ እንዲንር ማድረጉን ተከትሎ፣ ዋጋው ወደ መደበኛ መረጋጋት ለመመለስ ወራትን ሊወስድ ይችላል።

‎የዘርፉ የኃይል ባለሙያዎች እንደሚናገሩት፣ የዓለምን ፍላጎት ለማሟላት የነዳጅና የጋዝ አቅርቦቶች በነፃነት መሰራጨታቸውን እርግጠኛ ለመሆን የጭነት መርከብና የኢንሹራንስ ኩባንያዎች ስምምነቱ በጽኑ መሬት ላይ መቆሙን ማረጋገጥ ይፈልጋሉ።

‎​በኤስፒአይ አሴት ማኔጅመንት (SPI Asset Management) የሥራ ኃላፊ የሆኑት ስቲቨን ኢነስ ባወጡት ሪፖርት ላይ “የሆርሙዝ ወሽመጥ ዳግም መከፈት እንደ ማስተንፈሻ እንጂ ሙሉ በሙሉ የመጣ የሰላም ትርፍ (Peace dividend) ተደርጎ ሊወሰድ እንደማይችል ጠቁመው፥ ገበያው አሁን ላይ ያለውን የድፍድፍ ነዳጅ ስጋት ቀስ በቀስ ሊቀንስ ቢችልም፣ በዜና አርዕስት፣ በፊርማ እና በተግባር ደንቡን አክብሮ በሚንቀሳቀስ መንግሥት መካከል ያለውን ልዩነት አሁንም በዋጋው ላይ ማመጣጠን ይኖርበታል” ብለዋል።

‎በዘላለም ተስፋዬ