ቤተ ክርስቲያኗ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ባሻገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አገልግሎቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርሰቲያን የእምድብር ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉቃስ ገለፁ

ቤተ ክርስቲያኗ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ባሻገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አገልግሎቷን አጠናክራ እንደምትቀጥል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርሰቲያን የእምድብር ሀገረስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉቃስ ገለፁ

በሀገረ ስብከቱ ከአንድ መቶ አመት በላይ የዘለቀው የቅዱስ እንጦንዮስ ዓመታዊ ክብረ በዓል በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተ ክርሰቲያን የእምድብር ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ሉቃስ እንደገለጹት፤ ቤተ ክርስቲያኗ ከመንፈሳዊ አገልግሎቷ ባሻገር ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ባህላዊ አገልግሎት እየሰጠች ነው።

በሀገረ ስብከቱ ከ100 አመት በላይ እድሜ ያለው የቅዱስ እንጦንዮስ ገዳም በየአመቱ ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎችና ከአለም ሀገራት በመጡ ምዕመን እንደሚከበር ገልፀው ይህም መንፈሳዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።

የበዓሉ መከበር የአካባቢውን ባህልና እሴት ለማስተዋወቅ ፋይዳው የጎላ መሆኑን የገለፁት አቡነ ሉቃስ ገዳሙ በርካታ ቅርስና ታሪክ ያለው በመሆኑ መጠበቅ እና መንከባከብ እንደሚገባው አስረድተዋል።

በጉራጌ ዞን የእምድብር ከተማ አስተዳደር ባህልና ቱሪዝም ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ በሃሩ መጫ በበኩላቸው፤ በከተማ አስተዳደሩ ሰው ሰራሽ እና የተፈጥሮ መስህቦች መኖራቸውን ጠቁመው ሃይማኖታዊ በአላት የአካባቢውን የቱሪዝም ፍሰት በመጨመር ረገድ ጉልህ ሚና እንደሚኖረው ተናግረዋል።

የቅዱስ እንጦንዮስ አመታዊ ክብረ በዓል ለመታደም ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች እና ከውጭ ሃገራት እንደሚመጡም ጠቁመዋል።

ከተለያዩ አካባቢዎች የመጡ የክብረ በአሉ ታዳሚዎች በሰጡት አስተያየት፤ በመንፈሳዊ አገልገሎቶች ለመባረክ ወደ ገዳሙ እንደሚመጡ ጠቁመው በዚህም በገዳሙና በአካባቢው ያሉ እሴቶችን ለመጎብኘት እንደሚረዳቸው ተናግረዋል።

ገዳሙ እድሜ ጠገብ በመሆኑ በቅርስነት በመመዝገብ የበለጠ መንከባከብ፣ ማልማትና ማስተዋወቅ እንደሚገባም ገልፀዋል።

ዘጋቢ፡ ሔኖክ ተክሌ – ከወልቂጤ ጣቢያችን