የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ዝርፊያ ተፈፀመበት
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን በ2026 የዓለም ዋንጫ ዝግጅት ላይ እያለ ያልተጠበቀ እና አነጋጋሪ የሆነ የዘረፋ ወንጀል ገጥሞታል።
ቡድኑ በአሜሪካ ከፍሎሪዳ ወደ ካንሳስ ከተማ ሲጓዝ የቡድኑ የልምምድ እቃዎች የተጫኑበት ተሽከርካሪ ላይ ዘረፋ መፈጸሙ ተገልጿል።
የቡድኑ ወሳኝ የልምምድ ቁሳቁሶች፣ የጨዋታ ኳሶች፣ እና የቡድኑ አባላት (የጨዋታ ጫማዎችን ጨምሮ) መዘረፋቸው ተነግሯል።
በተለይም የቡድኑ አምበል ሃሪ ኬን እና የመሐል ሜዳው ኮከብ ጁድ ቤሊንግሃም የግል የጨዋታ ጫማዎች የዘረፋው ሰለባ መሆናቸው ከፍተኛ መነጋገሪያ ሆኗል።
የካንሳስ ከተማ ፖሊስ እንደገለጸው፤ በጉዳዩ ላይ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን እስካሁን ድረስ ከዘረፋው ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል።
የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን አባላት በስዊፕ ሶከር መንደር ልምምዳቸውን ለመጀመር ዝግጅት ላይ ነበሩ።
የኢንግሊሽ እግር ኳስ ማህበር አስፈላጊ ቁሳቁሶችን በአስቸኳይ ለመተካት ጥረት እያደረገ ቢሆንም ይህ ክስተት በቡድኑ ስነ-ልቦና ላይ ተጽዕኖ እንዳያሳድር ተሰግቷል።
ይህ አሳዛኝ ክስተት የተከሰተው እንግሊዝ በትልቁ የዓለም ዋንጫ ውድድር ከክሮሺያ ጋር የምታደርገውን የመክፈቻ ጨዋታ በጉጉት እየጠበቀች ባለችበት ወቅት ነው።
በአሰልጣኝ ቶማስ ቱሄል የሚመራው የእንግሊዝ ብሔራዊ ቡድን ከሚገኝበት ምድብ 12 ከክሮኤሽያ በተጨማሪ ከጋና እና ከፓናማ ጋር የሚጫወት ይሆናል።
ይህ ክስተት ቡድኑን ለጥቂት ቀናት የሚቆይ የሎጂስቲክስ ፈተና ውስጥ የከተተው ቢሆንም የቡድኑ ዝግጅት በታቀደው መሰረት እንደሚቀጥል እና ለክሮኤሽያው ጨዋታ ትኩረት እንደተሰጠ እየተገለጸ ይገኛል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የ2026 የዓለም ዋንጫ፡ የዛሬው የውድድር መርሐግብሮች
ማንቸስተር ዩናይትድ ማቲየስ ፈርናንዴዝን ለማስፈረም የዝውውር ጥያቄ ለማቅረብ እየተዘጋጀ ነው
የሞት ጥላን የተሻገረው ራውል ሂሜኔዝ